የምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ ከተማና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ ከተማና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ገለፁ
አዳማ ፤ ሐምሌ 17/2013(ኢዜአ) የምስራቅ ሸዋ ዞንና አዳማ ከተማ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት ዛሬ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሉዓላዊነት ምልክት ነው፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ፍላጎታችንን በምርጫ ካርዳችን ግልፅ አድርገናል፣ አፍሪካን ለአፍሪካውያን፣ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንቆማለን፣ የትግራይ ህዝብ አካላችን ጁንታው ጠላታችን፣ አባይ የኢትዮጵያ ህዝብ ምልክት ነው የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮችን አስተጋብተዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፤ ፤የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን ድጋፍና አጋርነት እንዲሁም የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ሙሌት የተሰማውን ደስታ ለመግለጽ አንድነቱን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል።
ባለፉት 27 ዓመታት ጁንታው የቀበረው ከፋፋይና አፍራሽ ተግባር ለመሻር አብሮነቱን አደባባይ በመውጣት ማስመስከሩን ገልጸዋል።
ከንቲባው ህወሃት የፈፀመው ክህደት የትግራይን ህዝብ የማይወክል ነው፤ ህዝብ ከመከላከያ ጎን በመቆም ግብዓተ መሬቱ እንዲፋጠን ማድረግ አለበት ብለዋል።
ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በሀገር ጉዳይ ላይ ያሳየውን አንድነት በማጠናከር የውስጥና የወጭ ጠላቶችን ማሳፈር እንዳለበትም አመልክተዋል።
"እኛ ከፋፋይ አጀንዳዎችንና የህዝብ አብሮነትና አንድነትን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችን በማምከን የሀገራችን የሉዓላዊነት ምልክት ከሆነው ከመከላከያ ጎን እንቆማለን ብለዋል።
ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሆን በማድረግ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መሳካቱና ህዝቡ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ ለውጤት እንደሚበቃ በተግባር ማሳየቱን ከንቲባው ገልጸዋል።