ቀጥታ፡

ግብጽና ሱዳን በግድቡ ላይ የሚያነሱት ተቃውሞ ኢትዮጵያ በቀጠናው ኃያል እንዳትሆን ከመስጋት የሚመነጭ ነው-- አክቲቪስት መካ አደም

ሀምሌ 16/2013 (ኢዜአ) "ግብጽና ሱዳን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚቃወሙት ኢትዮጵያ በቀጠናው ኃያል እንዳትሆን ከመስጋት የሚመነጭ ነው" ሲሉ ኢትዮጵያዊቷ የማህበረሰብ አንቂ መካ አደም ተናገሩ።

የማህበረሰብ እንቂዋ መካ አደም ለኢዜአ እንዳሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ግብጽን ጨምሮ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ተመጣጣኝ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በደለል የመሞላት እድላቸውን ዝቅ በማድረግ ደለሉን ለማስወገድ የሚያወጡትን ወጭ ይቀንሳል በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብርም ያጠናክራል ነው ያሉት።

ነገር ግን ግብጽና ሱዳን ይሄንን ጠንቅቀው እያወቁ ኢትዮጵያ በቀጠናው ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዳትሆን በማሰብ የግድቡን ግንባታ እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዋነኛ ዓላማ  የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ሳትጎዳ ከ60 ሚሊዬን በላይ ዜጎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑንም የማህበረሰብ አንቂዋ መካ አደም ተናግረዋል።

የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሶስቱ ሀገራት በተስማሙበት የመርሆች ስምምነት መሰረት መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያ የትኛውንም ሀገር ሳትጎዳ ህጋዊ መሰረትን ተከትላ ግድቡን እየገነባች መሆኑን አመላካች መሆኑን አብራርተዋል።

ግድቡን በተመለከተ ውጤታማ የዲሎማሲ ስራ ለማከናወን በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሶስቱ ሀገራት ህዝቦች ትብብርን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል

የግድቡን ዓላማና ለቀጠናው ያለውን ጥቅም ለመካከለኛው ምስራቅና አረብ ሀገራት በሚገባ በማስገንዘብ በግድቡ ላይ ትክክለኛ ምልከታ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ከ80 በመቶ በላይ አበርክቶ ቢኖራትም ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ በወንዙ የውሃ ድርሻ ላይ በተደረጉ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ውሃውን ለግብጽና ሱዳን ብቻ ያከፋፈሉ ናቸው።

በተቃራኒው ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ በውሃው ላይ ምንም ድርሻ እንዳይኖራት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም