ኢጋድ ለአካባቢያዊ ውህደት እንደሚሰራ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ ለአካባቢያዊ ውህደት እንደሚሰራ ገለፀ
ሀምሌ 16/2013 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት ኢጋድ ለክፍለ አህጉራዊ ውህደት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተቋሙ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ አጐራባች ህዝቦች መሀከል በጤና፣ በግብርናና በሌሎችም መስኮች መደጋገፍ እንዲኖር በማድረግ ክፍለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት እንዲኖር ይሰራል ብለዋል፡፡
ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኢትዮጵያ አዋሳኝ በሆነው የመንዴራ ክልል የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን የጐበኙ ሲሆን የሁለቱንም አገሮች ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ድጋፎችን ለመንዴራ ክልል አስተዳዳሪ አሊ ሮባ አስረክበዋል፡፡
ድርጅቱ ቀደም ሰል በኢትዮጵያ ለዶሎ አዶ እና ዶሎ ባይ ወረዳዎች ድጋፍ እንዳደረገ ተነግሯል፡፡
በመንዴራ ቆይታ ያደረጉት በኬንያ የኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በድንበሮች አካባቢ የሚገኙ ህዝቦችን የልማት ተጠቃሚ በማድረግ ለሰላም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ኢጋድ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ቡድኑ በመንዴራ የሚገኙ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን በኬንያ የኢፌዲሪ ኢምባሲ መረጃ ያሳያል ፡፡