ሆስፒታሉ 60 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶች ድጋፍ ተደረገለት

83

ጎንደር ሐምሌ 16/2013 (ኢዜአ) - የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 60 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶችን ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት ድጋፉ የተገኘው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ በተባሉ ኢትዮጵያዊ አስተባባሪነት በአሜሪካን ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ነው።

ሆስፒታሉ ትላንት ከተረከባቸው የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች መካከል የህሙማን አልጋ፣ ፍራሽና ዊልቸሮች ይገኙበታል።

ዘመናዊ የልብ መመርመሪያ፣ የጥርስ ህክምና መስጫ እንዲሁም የኮቪድ-19 ምርመራና ህክምና የሚሆኑ መሳሪያዎች እንደሚገኙበትም ጠቅስዋል፡፡
የሕክምና መሳሪያዎቹና መድሃኒቶቹ ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና ግብዓቶች እጥረት በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልሉ መሆናቸውንም  ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ከጎንደር ከተማና አጎራባች ዞኖች ለሚመጡ ሕሙማን አገልግሎት እየሰጠ ያለው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዓመት  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ታካሚዎችን ያስተናግዳል።

በተጨማሪም በተኝቶ ህክምና አገልግሎት በዓመት ለ28 ሺህ ህሙማን የህክምና ድጋፍ እንደሚሰጥ ተነግሯል።

በሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲውና የሆስፒታሉ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም