ሀገሪቱን ከጠላት ነፃ ለማውጣት የተሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን የልዩ ኃይል አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገሪቱን ከጠላት ነፃ ለማውጣት የተሰጣቸውን ግዳጅ በጀግንነት ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን የልዩ ኃይል አባላት ገለጹ
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 16/2013 (ኢዜአ) ሃገሪቱን ከማንኛውም ጠላት ነፃ ለማውጣት ተልዕኳቸውን በጀግንነት ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት ገለጹ።
የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ሁለተኛው ዙር ሃገራዊ ግዳጅ ሽኝትና የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ ስነ-ሥርዓትትናንት በሃዋሳ በተካሄደበት ወቅት አባላቱ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ህብረተሰቡ በተለያየ መንገድ የሚያደርገውን ድጋፍ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።
በግዳጁ ሃገራዊ ትልዕኮን ለመወጣት ሁላቸውም በፍላጎት ተነሳስተው መዘጋጀታቸውና በሃገራዊ ዘመቻውን በመቀላቀላቸውም ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከልዩ ሃይሉ አባላት መካከል ኮንስታብል ውብአለም ጎባቦ ፤ ሃገሪቱን ከማንኛውም ጠላት ነጻ ማውጣት ሙያዊ ግዴታዬ በመሆኑ ከመከላከያ ጎን በመሆን ሃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብላለች።
ሴትነቴ የሃገር ዳር ድንበር ከማስከበር አያግደኝም፣ የዚህ እድል ተካፋይ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ያለችው ኮንስታብል ውብአለም፤ ህብረተሰቡም ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ሃገር የሚያተራምሰውን የህወሃት ቡድን ለማስወገድ በሚካሄደው ዘመቻ የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፋለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ረዳት ኢንስፔክተር ጴጥሮስ ዘለቀ በበኩሉ፤ የለበስኩት ልብስና መለዮ ሃገር ስትደፈር ቆሜ እንዲያይ የሚያደርገኝ አይደለም ብሏል።
የክልሉ ልዩ ሃይል አባል ብሆንም ሃገር የሁላችንም በመሆኗ የሃገር ጉዳይ የኔም ነው ያለው ረዳት ኢንስፔክተሩ፤ የህወሃት ጁንታ ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እንዳስቆጣው ተናግሯል።
በዘመቻው በመሳተፉ እድለኛ መሆኑን ጠቅሶ እስከ መጨረሻው መስዋዕትነት ለመክፈልና የሃገሪቱን ዳር ድንበር ለማስከበር በሚካሄደው ትግል የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡
ሃገር ማለት ህዝብ ነው ያለው ኢንስፔክተር ጴጥሮስ ፤ ህብረተሰቡ በሚያስፈልገው ሁሉ ሰራዊቱን እንዲደግፍ አመልክቷል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የመሄድ ፍላጎት ኖሯት ሳይሳካ በመቅረቱ አዝና እንደነበር ያስታወሳችው ደግሞ ኮንስታብል ሎሚነሽ አየለ ናት፤
በሁለተኛው ዙር ግዳጁን በመቀላቀሏ መደሰቷን ገልጻለች።
ሴትነቴ ሳይገድበኝ ለሃገሬ እቆማለሁ ብዬ በወኔ ተሳስቼያለሁ፤ ሴቶች ከፍ ብለን ለሃገራችን ያለንን ክብር ለማሳየት የምንነሳበት ጊዜ በመሆኑ የደቡብን ልዩ ሃይሌ ወክዬ ተሰልፌያለሁ ብላለች።
ወጣት፣ አዛውንቱና ምሁሩም ሃገር የምትጠብቀውን ድጋፍ በማበርከት ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባና ከአቅጣጫው ለሃገራዊ ጥሪ የዘመተውን ሰራዊት እንዲደግፍም ጠይቃለች።
ሌላኛው የዘመቻው ተሳታፊ ኮንስታብል አማረ ለገሰ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያን ለመድፈር የሞከረውን አሸባሪው የህወሃት ቡድን መታገልና መደምሰስ ቀዳሚ እቅዳችን ነው ብሏል።
ሃገርን እንደ ሃገር ማስቀጠል የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሃላፊነት ቢሆንም ሰራዊቱ ሃገር ሲደፈር ቆሞ እንደማያይ ተናግሯል።
የትግራይ ህዝብ ነፃነቱን ለማረጋገጥ ጥቆማ በመስጠት የሃገር ጠላት የሆነውን ጁንታ ማጋለጥ እንዳለበትም አመልክቷል።
በሁለተኛ ዙር ሃገራዊ ግዳጅ ላይ ለመሳተፍ ለተዘጋጁ የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል የፖሊስ አባላት ትናንት ሽኝትና የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ በተካሄደበት ሥነ-ሥርዓት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳውና ሌሎችም የክልሉ አመራሮች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧለች።