ቀጥታ፡

በምዕራብ አርሲ ዞንና በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሰላም ግንባታን ተቋማዊ የሚያደርግ ስምምነት ተፈረመ

ሐዋሳ፣ ሐምሌ 16/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞንና ሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር የሰላም ግንባታን ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈረመ።

በሻሸመኔ ከተማ ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣የምእራብ አርሲ ዞንና የሻሸመኔ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት፣የዞኑና የከተማው ፖሊስ መምሪያዎችና የዞኑ አባገዳዎች ምክር ቤት ተወካዮች ናቸው።

ስምምነቱ ተቋማቱ በተናጠል የሚያካሂዱትን የሰላም ግንባታ ጥረት  የተቀናጀ፣  ዘላቂና ፍሬያማ እንደሚያደርገው ተመላክቷል።

ስምምነቱ የግጭት ማስጠንቀቂያና መከላከል፣ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ ችግሮችን በማጥናትና በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥን ያካትታል።

እንዲሁም ለግጭት መንስዔ ናቸው ተብለው የተሰበሰቡ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ ሥልጠና መስጠትንም ያጠቃልላል።

ተቋማቱ በሰላም፣ በሕግ የበላይነት፣ በማህበራዊ ልማት፣ የሃይማኖቶች ትብብር  ላይ አተኩረው እንደሚንቀሳቀሱና ተሞክሮውን እንደ ሞዴል በመውሰድ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት ውጥን መያዙ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሐን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዳሉት ስምምነቱ በሠላም ግንባታ ዙሪያ ለሚሰሩ ሥራዎች አስፈላጊ ነው።

"ስምምነቱ ሰላምን ለማስፈን የሚንቀሳቀሱ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአስተዳደር፣ የፖሊስና የፀጥታ አካላት በተናጠል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ወደ አንድ ለመሰብሰብና በመቀናጀት ውጤት ለማስመዝገብ ያስችላል" ብለዋል።

ጠቅላይ ጸሀፊው አክለው ሁሉም አካላት በሰላም ዙሪያ የሚያካሂዷቸውን ሥራዎች ወጪና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆኑ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምእራብ አርሲ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ አቡነ ሄኖክ በበኩላቸው ቀደም ሲል በዞኑና በሻሸመኔ ከተማ የደረሰው የሰላም እጦት ጠባሳ አሳርፎ ማለፉን ጠቅሰዋል።

"የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ባሉባት ሀገር ግጭትና ፀብ መከሰቱ አሳፋሪ ነው" ያሉት ሊቀ ጳጳሱ "የሕዝብ መሪዎች ኃላፊነታችንን ለመወጣት  አበክረን ልንሰራ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የዞኑ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አብዱልሐኪም ሐጂ ሁሴን በበኩላቸው በመደራጀት፣ እጅ ለእጅ በመያያዝ እንዲሁም በተጠያቂነትና በመናበብ ቢሰራ ሰላም ሳይደፈርስ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችል አስታውቀዋል።

ስምምነቱ የግጭት ምልክቶች ሳይናቁ ለማምከንና ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመካከሩና እየተወያዩ ለመፍታት  ዘርፈ ብዙ  ፋይዳ  እንዳለው ተናግረዋል።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ክፍሌ ጀልቀባ ስምምነቱ በከተማዋ  ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን   አመልክተዋል።

በከተማዋ  ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት የሃይማኖት መማክርት ጉባዔ አባላት ህዝባዊ መድረኮች በማዘጋጀትና ህዝቡን በማቀራረብ የከተማዋ ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም