ቀጥታ፡

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያልተመዘገቡ መመሪያዎች ተፈጻሚነት አይኖራቸውም - የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ

አዲስ አበባ ሃምሌ 16/2013 (ኢዜአ) በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያልተመዘገቡ መመሪያዎች በዜጎች ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸውና ኅብረተሰቡም "አልገለገልም" ብሎ ሊሞግት እንደሚገባ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገለጸ።

ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ተስፋዬ ዳባ ለኢዜአ እንዳሉት የአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ 1183/2012 ከወጣ ዓመት ቢያስቆጥርም በአስተዳደር ተቋማት ቸልተኝነት በአግባቡ ገቢራዊ አልተደረገም።

በወንጀል ሥነ ስርዓት ሕጉ የሚመሩት ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ ወይም የመከላከያና ደህንነት ተቋማት በዚህ የአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ አይካተቱም።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የአገሪቷን የውጭ ምንዛሬና የወለድ ተመን እንዲሁም ሌሎች ምስጢራዊ ጉዳዮች በተመለከተ መመሪያ ሲያወጣ በዚህ አዋጅ የተካተቱ ግዴታዎችን ለመተግበር አይገደድም እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ።

ይሁንና ከተጠቀሱት ተቋማት በቀር ሁሉም የአስተዳደር ተቋማት የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ መሰረት መመሪያዎቻቸውን ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እያስመዘገቡ አይደለም ብለዋል።

በአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ 1183/2012 መሰረት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያልተመዘገበ ወይም በተቋማቱ ድረገጽ ላይ ያልተጫነ መመሪያ ተፈፃሚነት አይኖረውም፤ ኅብረተሰቡም ባልተመዘገበ መመሪያ አልዳኝም ሊል ይገባል ነው ያሉት።

ባልተመዘገበ መመሪያ ሕዝብን ማገልገል የዜጎችን ሕገ መንግስታዊ መብት መጣስ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አዋጁን ተግባራዊ አለማድረግ ተጠያቂም ያደርጋል ሲሉ አክለዋል።

መመሪያ አስመዝግበው 'ያላችሁ መመሪያ ያስመዘገባችሁት ብቻ ለመሆኑ የማረጋገጫ ደብዳቤ ላኩ' ተብለው ከተጠየቁ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አንድም ምላሽ የሰጠ የለም ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

ከዚህ በኋላ መመሪያ ከጠረጴዛ ስር እያወጡ "ይሄ ይጠቅማል ይሄ አይጠቅምም" የሚል አሰራር አይኖርም ያሉት አቶ ተስፋዬ አዋጁን በትክክል በማይተገብሩ የመንግስት ሹማምንት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር የሚሰራ ዳይሬክቶሬት እንዳለው ጠቅሰው ተቋማት ተጠያቄ እንዲሆኑ ለማድረግ ዝግጅታችንን ጨርሰናል ብለዋል።

አዋጁ ከፀደቀ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም እስካሁን የተመዘገቡ መመሪያዎች የፌዴራል 802፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 67 ሲሆኑ የድሬዳዋ አስተዳደር አንድም መመሪያ አላስመዘገበም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም