ቀጥታ፡

የአሜሪካን ጣልቃ ገብነትና በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ የሚቃወም ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16/2013 (ኢዜአ) አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና የሚቃወምና በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎች የሚደርስባቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚያወግዝ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ሕብረት ዋና መስራች አቶ ቢኒያም ጌታቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት ሰላማዊ ሰልፉ የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ/ም በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትና የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ይካሄዳል።

በሰልፉ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እያደረገች ያለው ጣልቃ ገብነትና ጫና ተገቢ አለመሆኑን የሚገልጽ ተቃውሞ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት።

በተጨማሪ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለው ስቃይና እንግልት እንዲቆም ጥሪ ይቀርባል ብለዋል።

በሰልፉ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶችና ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ ነው አቶ ቢኒያም ያስረዱት።

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎች ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልገው በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለወገኖቹ ድምጽ በመሆን አጋርነቱን እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት ዜጎችን ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት አቶ ቢኒያም፤ መንግስት ዜጎችን ለመታደግ  ከዚህ በበለጠ ትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

በዋሺንግተን ዲሲ የሰላምና አንድነት ግብረ ሃይል ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መልዐከ ሕይወት በበኩላቸው የሰልፉ አስተባባሪዎች ለአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትና ለሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ደብዳቤ እንደሚያስገቡ ገልጸዋል።

ለስቴት ዲፓርትመንት የሚገባው ደብዳቤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና እንድታቆምና የውጭ ፖሊሲዋን ዳግም እንድትመረምር እንዲሁም ኢትዮጵያና አሜሪካ መርህ ላይ በተመሰረተ ግንኙነት በጋራ ጉዳዮች ላይ መስራት እንዳለባቸው መልዕክት የያዘ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የሚያደረሰውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲያቆምና የዜጎች መብት ማክበር እንደሚገባው መልእክት የያዘ ደብዳቤ ለኤምባሲው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሰላማዊ ሰልፉ በመሳተፍ አጋርነቱን እንዲያሳይም ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የፊታችን እሁድ ሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም  በዋሺንግተን ዲሲ ሚሞሪያል ፓርክ ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ለሌሎች የጸጥታ ተቋማት አጋርነት መግለጫና ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ይካሄዳል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመከለካያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ ተቋማት አገርን ለመጠበቅ እያከናወኑት  ላለው ተግባር ምስጋናና እውቅና የሚሰጥ ይሆናል ነው ያሉት።

በተጫማሪ የሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት አስመልክቶ የደስታ መልዕክት እንደሚተላለፍም አቶ ጣሰው ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በአሁኑ ሰዓት በጋራ በመሆንና በትብብር በመስራት ኢትዮጵያ እየደረሰባት ያለውን ጫና ለመመከት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ዲያስፖራው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ እንዲሁም በየሚኖርበት አካባቢ ያሉ ባለስልጣናት በአካል በማግኘት በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ የማስገንዘብ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ይህ ተግባርም ወደፊት በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ለሀገራቸው ጉዳይ በጋራ መቆም እንዳለባቸው ገልጸው፤ መረጃዎችን ከሚመለከተው አካል ብቻ በመቀበልም ከሐሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ መክረዋል።

መንግስት ከዲያስፖራው ጋር ያለውን ግንኙነት በሚያጠናክርበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራም ነው ያሳሰቡት።

በዋሺንግተን ዲሲ የሚካሄደውን ሰልፍ ያዘጋጁት በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ግብረ ሃይል ፣የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወጣቶች ሕብረትና ሌሎች በአሜሪካ የሚገኙ ተቋማት በጋራ በመሆን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም