ቀጥታ፡

የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተገለፀ

አዲስ አበባ  ነሀሴ 2 / 2010 በኢትዮጵያ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መጀመሩ በህዝቦች መካከል መቀራረብን ከማጠናከር ባሻገር አገራዊ አንድነትን፣ መቻቻልንና መተሳሰብን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተገለጸ። ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ የሚልቅ ወጣቶች ለመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተሰማርተዋል። በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለተሰማሩት ፈቃደኞች የሥራ መመሪያም ተሰጥቷል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ ወጣቶቹ ከክልሎቻቸው ወጥተው ለሌሎች ክልል ህዝቦች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸቱ ለአገራዊ ሰላም፣ አንድነትና እድገት ወሳኝ የሆነውን የህዝቦች መፈቃቀርንና መተሳሰብን ለማጠናከር ያግዛል። ወጣቶቹ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አማካኝነት ከክልሎቻቸው ውጪ  መጓዛቸው የሌሎች ማህበረሰብ ክፍሎችን ባህልና አኗኗር በአግባቡ እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል፤ በዚህም "የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጎልበት የሚያግዝ እድል ይፈጥራል" ሲሉም አቶ ርስቱ ገልፀዋል።   ይህም ከሌሎች ተመሳሳይ የህዝብ ንቅናቄዎች ጋር ሲደመር አገራዊ አንድነትንና መተሳሰብን ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።  የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱም በወጣቶቹ ዘንድ "ትልቅ አገራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ስሜትን ለመፍጠርም ያግዛቸዋል" ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም (ዶክተር) ለወጣቶቹ ሽኝት ሲያደርጉ በሰጡት ማሳሰቢያ ወጣቶቹ በበጎ ፈቃድ ተግባራቸው አንድነትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ማሳሰባቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የበጎ ፍቃደኞቹ በትምህርት፣ በአካበቢ ንፅህና ጥበቃ፣ ተላላፊ በሽታን በመከላከል፣ ደም በመስጠት፣ በትራፊክ አደጋና የአየር ለውጥ ችግሮችን  በመከላከል ጉዳዮች ላይ በማተኮር እንደዚሁም በማስተማር ተግባራት ይሰማራሉ። የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች  አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በዚሁ አጋጣሚም ከማህበረሰቡ ጋር በመቀራረብ ማንነታቸውን በቅርበት ለመረዳት እና በህዝቦች መካከል አንድነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ተግባራት ተግተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።  በበጉ ፍቃድ አገልግሎት የተሰማራው የአዲስ አበባ ወጣት ቢኒያም ስዩም እንደተናገረው  በበጎ ፍቃድ ፕሮግራሙ ደም በመስጠት  ትምህርት በመስጠት  ኤች አይቪ ኤድስ ላይ  በማስተማርና  ችግኝ ተከላም እንደሚያካሄድ ተናግሯል፡፡  “ባህላቸውን በጥልቀት የማወቅ ፍላጎት አለኝ አሁን የሚሄድበት አካባቢ ላይ ብዙ ነገሮችን ይዤ እመጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ያለችው ደግሞ ከጉራጌ ዞን በበጎ ፍቃዱ የተሳተፈችው  አልማዝ አስፋው ነች አንድ ሰው ተደስቶ ማየት ታላቅ ደስታ ነው ያለው ከአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ተወላጅ የሆነው  አማኑኤል ደስታው በበጎ ፍቃዱ የተጠናከረ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብሏል በወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃደኞች አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ቁጥራቸው አንድ ሺህ ገደማ ሲሆን፤ የሚሰጡት አገልግሎት እስከ ነሓሴ አጋማሽ እንደሚቆይ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ትናንት ለወጣቶቹ የሥራ መመሪያ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን የመረዳዳትና የመቻቻል ባህል ለማስቀጠል ወጣቱ ኃላፊነቱን አንዲወጣ ጥሪ  አቅርበዋል። የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአገሪቷ በዩኒቨርስቲ ምሩቃንና በመማር ሂደት የሚገኙ ወጣቶች ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በአገሪቷ በየዓመቱ በክረምት የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎቶች የሚሰጡት ሲሆን፤ በአሁኑ የበጎ ፈቃደኞች አገልግሎት ወጣቶች ከክልላቸው በመውጣት ወደ ሌሎች ክልሎች ሄደው የሚያገለግሉ መሆናቸው ታውቋል። የዚህ ዓይነቱ መርሃ ግብር ተሳታፊዎች ቁጥር በመጪዎቹ ዓመታት በማስፋት በቋሚነት እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም