በድሬዳዋ ኮሮናን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል-- ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ

64

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 16/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ኮሮናን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ አሳሰቡ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ኮሮናን በመከላከሉ ስራ ግንባር ቀደም ሚናቸውን ለተወጡ የህክምና ተቋማትና ግለሰቦች ትናንት ዕውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ምክትል ከንቲባው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋማት ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከልና ህሙማንን ለማዳን ላደረጉት  ተጋድሎ ምስጋና ይገባቸዋል።

"ኮሮናን ለመከላከል ከአስተዳደሩ ጎን በመሰለፍ በዕውቀት ፣ገንዘብና ቁሳ-ቁሶች ድጋፍ ላደረጋችሁ በሙሉ አስተዳደሩ ምስጋና ያቀርባል "ብለዋል።

በአስተዳደሩ ኮሮናን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አቶ አህመድ አሳስበዋል ።

የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ  በበኩላቸው፤የምስጋናና ዕውቅና ስነ-ስርዓቱ የተዘጋጀው የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከርና በህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን መቀዛቀዝ ለመለወጥ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።


ዕውቅናና ሽልማት የተሰጣቸው ተቋማት እንደገለጹት፤  ዕውቅናው ለዜጎች ጤንነት መስዋዕት የመክፈል ተቀዳሚ ተልዕኮአቸውን ያጠናክርላቸዋል ።


በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኘው አስተያየቱን የሰጠው የዶክትሬት ተማሪው ዓቢይ ሠራዊት፤ ከኮሮና በሐኪሞች ርብርብ ህይወታቸው መትረፉን አስታውሶ፤ "ለህይወታቸው ሳይሳሱ የሰውን ነብስ ለማዳን ሌት ተቀን ለሚለፉ ምስጋና ማቅረብ ያንስብኛል" ብሏል።

"በኮሮና መያዝ ምን ያህል ከባድ መሆኑን የሚያውቀው ከሞት የተረፈው ብቻ ነው" ያለው ተማሪ ዓቢይ፤ የጤና ባለሙያዎችና ሕዝቡ ራሱን ከወረርሽኙ ሳይዘናጋ እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላልፏል።

በአስተዳደሩ ኮሮናን በመከላከሉ ስራ ግንባር ቀደም ሚናቸውን ለተወጡ  የመንግሥትና የግል ጤና ተቋማት እንዲሁም  ሃብትና ንብረታቸውን ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦች  የዋንጫ ሽልማት ፣ የዕውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋና ምክትል ከንቲባው አበርክተውላቸዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም