ቀጥታ፡

ሀገርን የማዳን ተልዕኮ ተቀብሎ ወደ ግዳጅ ለተንቀሳቀሰው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ልዩ ሃይል ሽኝት ተደረገለት

አሶሳ ሐምሌ 16 / 2013 (ኢዜአ) ሃገርን የማዳን ተልዕኮ ተቀብሎ የአሸባሪውን ጁንታ ትንኮሳ ለመመከት ወደ ግዳጅ ለተንቀሳቃሰው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይል ትናንት ምሽት ይፋዊ የሽኝት ስነ-ስርዓት ተደረገለት፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በወቅቱ እንዳሉት ልዩ ሃይሉ ወደ ግዳጅ የሚሰማራው የጁንታውን ሀገርን የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ ለቀረበው ሃገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ነው።

"ጁንታው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዶ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል መስዋዕትነታችን ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

"የማይታለፍ ችግር የለም" ያሉት አቶ አሻድሊ "አንድነታችን በማጠናከር ሽብርተኛው ቡድን ይወገዳል" ሲሉ ልዩ ሀይሉን አበረታተዋል፡፡

"በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ያለውን የጸጥታ ችግር በማሶገድ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በጋራ የጀመርነውን ጥረት እንድንወጣም አደራ እላለሁ " ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል ።

ያለመስዋዕትነት የሚገኝ ሃገር አለመኖሩን ገልጸው "በክልሉ ሠላም ለማስጠበቅ ስታከናውኑ የነበረውን ትግል እንደምታጠናክሩ እምነት አለኝ" ብለዋል፡፡

ልዩ ሀይሉ ስነ-ምግባርን በመላበስ የህግ ማስከበር ስራውን በስኬት እንዲወጣ መልእክት አስተላልፈዋል ።

የክልሉ መንግስት በበጀትም ሆነ በአስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አቶ አሻድሊ አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሃመድ በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ሽኝቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

"የልዩ ሀይሉ ወደ ግዳጅ መሰማራት የሀገር መከላከያ አቅምን በማጠናከር የጁንታውን ርዝራዦች ለመበተን ያለንን ሀገራዊ አቋም ያጠናክራል" ብለዋል፡፡

የክልሉ ጸረ-ሽምቅ ልዩ ጥበቃና አድማ ብተና መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር ኢዶሳ ጎሹ በበኩላቸው "ትናንት ስንከፍል የነበረውን መስዋዕትነት ዛሬም በመድገም ሃገራችንን ከሽብርተኛው ቡድን ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ" ብለዋል፡፡

ሃገራዊ ተልዕኮውን ተቀብለው ለግዳጅ ከተዘጋጁት የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት መካከል ኢንስፔክተር ሃዋ አሚር "የተሰጠኝን ግዳጅ በወኔ እወጣለሁ" ብላለች፡፡

ኢንስፔክተር አበራ ገርቢ በበኩሉ "ጁንታው በሃገራችን ላይ እያደረሰ የሚገኘው ጥፋት ልባችን የሰበረ ነው" ሲል ገልጻል፡፡

"ጁንታውን ባለበት ተገኝተን ለመደምሰስ ዝግጁ ነን"ሲል ለኢዜአ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም