ቀጥታ፡

ከተፎካካሪዎቻችን አንጻር በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ያገኘነው ውጤት ብዙ የቤት ስራ ሰጥቶን ያለፈ ነው- ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ

አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2010 ኢትዮጵያ በአፍሪካ አዋቂዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከተፎካካሪዎቿ አንጻር ያገኘችው ውጤት የቤት ስራ ሰጥቶን ያለፈ ነው ሲል የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ገለጸ። በናይጄሪያ አሳባ ከተማ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የተዘጋጀ የአቀባበልና የሽልማት ፕሮግራም ዛሬ ማለዳ በአራራት ሆቴል ተካሄዷል። የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከሐምሌ 25 እስከ 29 ቀን  2010 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ64 አትሌቶች ተወክላ በ19 የውድድር አይነቶች ተካፍላለች። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅ፣ ሶስት የብርና አምስት የነሐስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያ አምስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን ማጠናቀቋ አይዘነጋም። በናይጄሪያው የአፍሪካ የአዋቂዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው የሜዳሊያ ብዛትና ደረጃ በደቡብ አፍሪካ ደርባ ከተማ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው 20ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከተገኘው የተሻለ ነው። ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካው ሻምፒዮና አንድ ወርቅ፣ ሁለት የብርና ሶስት የነሐስ በጠቅላላ ስድስት ሜዳሊያ በማግኘት ስምንተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ እንዳለው የተገኘው ውጤት ከሁለት ዓመት በፊት ከደቡብ አፍሪካ ከተገኘው ውጤት ጋር ሳይሆን ከተፎካካሪዎችን አንጻር መታየት ይገባዋል። ከተፎካካሪዎቻችን አንጻር ያገኘነው ውጤት ከሌሎች አገራት ጋር ያለንን ልዩነት ያሳየና ብዙ የቤት ስራ ሰጥቶን ያለፈ እንደሆነ ነው ሻለቃ ሃይሌ የገለጸው። በተለይም በአጭር ርቀት፣ በውርወራና ዝላይ የተመዘገበው ደካማ ውጤት በውድድር አይነቶቹ ላይ የሚገባንን ስራ እንዳልሰራን የሚያመላክትና በቀጣይ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባን የሚያሳይ እንደሆነም ተናግሯል። በውድድር አይነቶቹ ውጤታማ ለመሆን በአሰለጣጠን፣ በልምምድና ቴክኒክ ስራዎች በመለወጥ ጊዜው ከደረሰበት ሁኔታ አንጻር መስራት እንደሚያስፈልግም አስታውቋል። ለዚህም አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና አመራሮች ከአሁኑ ያለውን ነገር በማሻሻል በቀጣይ ውድድሮች ላይ ውጤታማ መሆን እንደሚገባም አሳስቧል። የአትሌቶች ስነምግባርና የቡድን መንፈስ ጉዳይም ወደ ፊት ሊታረምና ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም አንስቷል። "100 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር በተለያዩ ርቀቶች ብቁ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት አያቅታትም" ያለው ሻለቃ ሃይሌ፤ ሁሉም አካል በጋራ ከሰራ ኢትዮጵያ በማትታወቅባቸው ስፖርቶች ጭምር ውጤት የማታመጣበት ምክንያት የለም ብሏል። በ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች አትሌት የኋልዩ በለጠው ያመጣችው የወርቅ ሜዳሊያና በከፍታ ዝላይ ሴቶች አርያት ዲቦ ያገኘችው የነሐስ ሜዳሊያ በማሳያነት ተጠቅሷል። በቀጣይ ዓመት በኳታር ዶሃ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ከሁለት ዓመት በኋላ ጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ኦሎምፒክ ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ኢትዮጵያን በውጤታማነት ማስጠራት እንደሚገባም ገልጿል። የአትሌቲክስ ቡድኑ መሪ አቶ አድማሱ ሳጂ ከሰራነው ልምምድና ካደረግነው ዝግጅት አንጻር የተገኘው ውጤት ያን ያህል አስከፊ እንዳልሆነና ለወደፊቱ ግን ትምህርት የሚሆን መሆኑን ገልጸዋል። የነበረውም ከፍተኛ ሙቀት ለአትሌቶቻችን ፈታኝና አስቸጋሪ እንደነበርም ተናግረዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በአትሌቲክሱ በተለያዩ ርቀቶች ያለው ተፎካካሪነት እየተቀየረ መምጣቱን ከሻምፒዮናው መማር እንደሚቻልም ገልጸዋል። የውድድሩ አዘጋጅ በምግብ፣ በትራንስፖርትና በውድድር በተሻለ አቅም ከመምራትና ከሌሎች አገልግሎቶች አንጻር የሰራው ስራም "ፍጹም ያልተደራጀና ቅንጅት የጎደለው" እንደበርም አመልክተዋል። በውድድሩ ተሳትፈው ሜዳሊያ ላለመጡ አትሌቶች 3 ሺህ ብር እንዲሁም የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ 25 ሺህ ፣የብር ሜዳሊያ ላመጡ 18 ሺህና የነሐስ ሜዳሊያ ላመጡ የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል። ከአራት እስከ ስድስት በመውጣት ዲፕሎማ ላመጡ አትሌቶች የ6 ሺህ ብር ሽልማት የተሰጣቸው ሲሆን በአጠቃላይ ለልዑካን ቡድኑ ከ700 ሺህ ብር በላይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎች ለአትሌቶቹ የተዘጋጀውን ሽልማት ሰጥተዋል። አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ፣ አትሌት ወይንሸት አንሳና አትሌት ጌታነህ ሞላ በናይጄሪያ ባስመዘገቡት ውጤት ጳጉሜ 3 እና 4 ቀን 2010 ዓ.ም በቼክ ሪፐብሊክ ኦስትራቫ ከተማ በሚካሄደው ሶስተኛው የአህጉራት የአትሌቲክስ ውድድር (IAAF Continental Cup) ላይ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል። በናይጄሪያ አሳባ ከተማ ሲካሄድ በቆየው 21ኛው የአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና አዘጋጇ ናይጄሪያ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። የናይጄሪያውን ጨምሮ ኢትዮጵያ እስከ አሁን በተሳተፈችባቸው ሻምፒዮናዎች 42 የወርቅ፣ 50 የብርና 59 የነሐስ በድምሩ 151 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም