ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባቱን ተከትሎ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች መገደላቸው ተገለጸ

ሐምሌ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባቱን ተከትሎ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች እንደተገደሉ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ገለጸ።

በማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበትን ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡን አስታውሷል።

ኤጀንሲው በማይ-ጸምሪ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን አስመልክቶ መግለጫ  አውጥቷል።

በመግለጫው ያጋጠሙ ችግሮችን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ እየተቋቋመ ያለውን መጠለያ ጣቢያ ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል።

“ከግጭቱ ቀጠና ለወጡ ስደተኞች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እና አገልግሎቶችን በማደራጀት ላይ እንገኛለን” ያለው ኤጀንሲው፤ ይህንን ለማሳካትም ትምህርት ቤቶችን በጊዜያዊ መጠለያነት ለመጠቀም ከአከባቢው የመንግሥት ኃላፊዎች ፈቃድ እና ሙሉ ድጋፍ ማግኘቱን ገልጿል።

ጥቂት አጋሮች ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ ጠቅሶ፤ አስፈላጊ የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ አካባቢው የተጓጓዙ መሆኑን አመልክቷል።

ስደተኞችን መቀበል፣ በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች ማስጠለል እና ትኩስ ምግብ ማቅረብ የተጀመረ ቢሆንም ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታ አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሄዱ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ አስገንዝቧል።

“ህወሃት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባቱን ተከትሎ እስካሁን ድረስ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች እንደተገደሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ተገኝተዋል” ብሏል።

“ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ሕግ በመጣስ የህወሃት ታጣቂዎች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከባድ መሣሪያዎችን የተከሉ ሲሆን ቀጣይነት ያለው የታጣቂ እንቅስቃሴ እና አልፎ አልፎም የተኩስ እሩምታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ” ሲል አመልክቷል።

በተጨማሪም ለሰብአዊ አገልግሎት እንዲውሉ የተዘጋጁና የተቋቋሙ ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ አምቡላንሶችን እና መሰረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ እንደሆነ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ጠቅሷል።

በዚህም ምክንያት ቢያንስ ሁለት ስደተኞች በጤና አገልግሎት እጥረት መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን እናቶች አስጊ በሆነ ሁኔታ እየወለዱ እንደሚገኙም አመልክቷል።

“የዓለም የምግብ ፕሮግራም መጋዘኖችን ጨምሮ የኤጀንሲያችን እና የሌሎች አጋሮች ንብረቶች እንደተዘረፉ መረጃዎች ደርሰውናል” ያለው የኤጀንሲው መግለጫ፤ ስደተኞች ለጦርነቱ የሚውል በዓይነትና በገንዘብ መዋጮ እንዲከፍሉ እየተገደዱ እንደሆነም ገልጿል።

ስደተኞቹ ከግጭቱ አካባቢ ለመልቀቅ የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ በህወሃትመከልከሉን ገልጾ፤ ስደተኞቹ የሚገኙበት ሁኔታ ከእገታ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ጠቅሷል።

በተቃራኒው ስደተኞችን በጅምላ ወዳልታወቁ ቦታዎች በኃይል የማጓጓዝና እና የተወሰኑትን በህዳር ወር ችግሩ እንደተከሰተ በራሳቸው በህወሃት ታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ተዘጉት ህጻፅና እና ሽመልባ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲዛወሩ የማድረግ ሙከራዎች እንዳሉም አመልክቷል።

“እስከ ዛሬ ድረስ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ወደ ማይ-ጸምሪ ወደ ሚገኙት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መግባትም ሆነ ለስደተኞች አገልግሎት መስጠት አልቻሉም” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች ደህንነት ለመጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጦ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈፀሙ በጭካኔ የተሞሉ ወንጀሎችን በማያሻማ ሁኔታ እንዲያወግዝ ጥሪውን አቅርቧል።

“በተጨማሪም ስደተኞች ከሚገኙበት አደገኛ ሁኔታ እና የእገታ አዝማሚያ ለመታደግ የምናደርገውን ጥረት እንዲደግፍ እና በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለማጣራት የምናደርገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል በመግለጫው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም