አንድነታችንን የሚያጠናክረው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን እንቀጥላለን - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን የሚያጠናክረው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን እንቀጥላለን - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 15/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የመዲናዋ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ በመስቀል አደባባይ በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች የግድቡ የ2ኛ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያውያን ያለማንም እርዳታና ድጋፍ በራሳቸው አቅም ያለሙትን ማሳካት እንደሚችሉ ያመለከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ አሸንፋ በድል ትሻገራለች ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖ በጋራ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን መጻኢ ተስፋ መሆኑን ገልጸው፤ የግድቡ እውን መሆን በተለይ በጭስ ለሚሰቃዩ እናቶች እፎይታን እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።
ከዚህ አኳያ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከኢትዮጵያ የተሻለ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እያላቸው የግድቡን ግንባታ መቃወማቸው አግባብ አለመሆኑንም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
በመሆኑም የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የኢትዮጵያውያን የመልማት ፍላጎት እውን እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።