አሸባሪው ሕወሃት በህጻናት ህይወት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተውተረተረ እንደሚገኝ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ሕወሃት በህጻናት ህይወት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተውተረተረ እንደሚገኝ ተገለጸ
ሐምሌ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) "አሸባሪው ህወሃት በህጻናት ህይወት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተውተረተረ ነው" ሲል መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለኢዜአ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በአፋር ክልል አለሌ ሱሉላ አካባቢና በአማራ ክልል በቆቦ ግራና ቀኝ ለትንኮሳ የመጣው ሃይል ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል።
አሸባሪው ህወሃት ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ያልደረሱትን ህጻናት እያስገደደ ለሦስት ቀናት ያልበለጠ ሥልጠና በመስጠት ወደ ውጊያ አስገብቶ መቋቋም በማይችሉት ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን ነው መከላከያ ሚኒስቴር የገለጸው።
“በጦር ሜዳ ካሰለፋቸው ህጻናት ድል አገኛለሁ ብሎ በማሰብ እያስጨረሳቸው ይገኛል” ያለው ሚኒስቴሩ፤ ይህ ሳይበቃ በውጊያ የተገደሉትን ህጻናት ሬሳ በመሰብሰብ “የኢትዮጵያ መንግስት ሠራዊት ገደላቸው” ብሎ በውጊያ ያስጨረሳቸውን ህጻናት ሬሳ መነገጃ ለማድረግ የተለመደውን የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ሬሳቸውን ኹሓ ላይ ሰብስቦ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም በመወሰን ከትግራይ መውጣቱን ካሳወቀ በኋላ የአሸባሪው ሃይል ሠራዊቱን እየተከተለና እየተነኮሰ እርሱ በፈጠረው ውጊያ እንደተመታ የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ “ሠራዊታችን የራሱን የማጥቃት እርምጃ አልወሰደም” ብሏል።