ቀጥታ፡

በቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ላይ በደል አድርሰዋል የተባሉ የሐይማኖት አባቶች ከሥራ ተባረሩ

አዲስ አበባ ነሓሴ 2/2010 በቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ላይ "በደል አድርሰዋል" የተባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ አገረ ስብከት አስራ አራት የሐይማኖት አባቶች ከሥራ ተባረሩ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር በመሆን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምነህ ዘውዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሐይማኖት አባቶቹ የተባረሩት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮቹ ለኮሚሽኑ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት በተደረገው ማጣራት ነው። ሦስት መቶ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ ካህናት "አላግባብ ከሥራ ማባረር፣ ማገድ፣ ደመወዝ መቀነስ፣ ያልተገባ ዝውውርና መሰል አስተዳደራዊ በደሎች ደርሶብናል" በማለት ክስ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። እንደ አቶ ወንድምነህ ገለጻ ኮሚሽኑ የቀረበለትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ከቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያሪክ ጋር ምክክር ተደርጎ ጉዳዩን የሚያጣራ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተከናወነ ሥራ ነው። አጣሪ ኮሚቴው በአንድ ወር ውስጥ ባደረገው ማጣራት "በአገልጋይ ካህናቱ ላይ ከፍተኛ አስተዳደራዊ በደል መድረሱንና ላለፉት ሁለት ዓመት ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለው መጉላላት እንደደረሰባቸው ለኮሚሽኑ ያቀረበው ሪፖርት ያስረዳል" ብለዋል። በዚሁ መሠረት በቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ላይ በደል የፈጸሙት ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የተደረገ ሲሆን፤ አገልጋይ ካህናቱም የሚገባቸው ጥቅማ ጥቅም ተከብሮላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መወሰኑን ገልጸዋል። አዲስ የተሾሙት በቤተ ክርስቲያኗ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መምህር ይቅርባይ እንዳለ እንደገለጹት፤ 'በካህናቱ ላይ በደል አድርሰዋል' የተባሉት የቀድሞ የአገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሐይማኖት አባቶች በሙሉ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ ተደርጓል። በደል የደረሰባቸው ካህናትም የሚገባቸውን የደረጃና የደመወዝ እርከን ተጠብቆላቸውና በቤተክርሰቲያኗ በተገኙ ክፍት የሥራ ቦታዎች ላይ እንዲመደቡ መደረጉን ገልጸው፤ ውዝፍ ደመወዛቸውም እንዲከፈላቸው መወሰኑን ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም