ቀጥታ፡

በሕዳሴው ግድብ ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ሊሰራ ይገባል --ምሁራን

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ሐምሌ 15/2013 በሕዳሴው ግድብ ላይ ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ሊሰራ ይገባል ሲሉ በደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራን አስታወቁ።

ኢዜአ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅን አስመልክቶ ከምሁራኑ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዶክተር አስማማው አዳነ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያላት አቋም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው።

በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ በሚደረጉ ድርድሮች የተፋሰሱ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጎን ሊሰለፉና ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል ።

"የዓባይ ውሃ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት ዳኝነት መታየት ሲገባው ግብፅና ሱዳን ባልተገባ መንገድ ለፀጥታው ምክር ቤት ማቅረባቸው ተገቢነት የለውም" ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ያወጣውን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍታሃዊ የውሃ አጠቃቀም መርህን መከተል ለተፋሰሱ ሀገራት የተሻለ መሆኑን አመልክተዋል ።

በአሁኑ ወቅት ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በሀገር ላይ የተቃጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመቀልበስ ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ የውጭ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ግብጽ ከፍተኛ የከርሰ ምድር የውሃ ክምችት እንዳላት ያወሱት ዶክተር አስማማው የህንድ ውቂያኖስ ውሃን በቴክኖሎጂ በማከም ለልማት ማዋል እንደምትችልም ጠቅሰዋል።

"ግብጽ አማራጭ ሳታጣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በዓባይ ወንዝ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ እየተከተለች ያለው ያልተገባ አካሄድ ዛሬም ከቅኝ ግዛት እሳቤ እንዳልወጣች ያሳያል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ 85 ከመቶ የውሃ አበርክቶ እያላት ሃብቷን አልምታ ለመጠቀም እንዳትችል እየተደረገ ያለው ግፊትና ጫና በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ህግ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ በዳኔ በበኩላቸው "የሕዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት የምዕራባዊያንን እኩይ ሴራ በማክሸፍ የኢትዮጵያን አሸናፊነት በግለጽ ያሳየ ነው" ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት ግብፅ ሙግት ውስጥ የገባችው የዓባይ ውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል ሳይሆን በጎርፍ ተጠርጎ የሚሄደው ለም አፈር ይቀርብኛል በሚል ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ መንግስት የዲፕሎማሲውን ሥራ ማጠናከር እንዳለበት የጠቀሱት አቶ አበበ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችና ኢትዮጵያዊያን ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

"የላይኛውም ሆነ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲጎለብት ማድረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት የግድቡ አካባቢ እንዳይራቆትና በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል ጭምር ጠቀሜታ ስላለው የተፋሰሱ ሃገራት ኢትዮጵያን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ የዓባይ ገባር የሆኑ ጣና ሐይቅ፣ ጀማ፣ ደዴሳና ባሮን ጨምሮ ሌሎች ወንዞችን በመንከባከብ በልማቱ ከመንግስት ጎን እንዲሰለፍ ምሁራኑ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም