የተሳሰረ ማንነት - ኢዜአ አማርኛ
የተሳሰረ ማንነት
ዳግም መርሻ/ኢዜአ/ እ.አ.አ በ1860 አካባቢ ከአጠቃላዩ የፈረንሳይ ህጻናት ግማሽ ያህሉ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የፈረንሳይ ዜጎች አየተነጋገሩበትና እየተግባቡበት ላለው የፈረንሳይኛ ቋንቋ እንግዳ እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ። ከፈረንሳይ ዋና ዋና ከተሞች ውጭ ባሉ ስፍራዎችም ሀገረ ፈረንሳይ የልዩ ልዩ አይነት ቋንቋዎች፣ የአነጋገር ፈሊጦች እና የመገበያያ ገንዘቦች መነሀሪያ ሀገር እንደነበረች በታሪክ ድርሳናት ተጽፏል። ከአንድ የተወሰነ የመኖሪያ ክልል ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር እምብዛም ያልተለመደ ነገር ከመሆኑ በላይ አንድ ሀገረ ብሄረ መንግስት(Nation State) የሚለው ጽንሰ-ሀሳብም በህዝቡ ውስጥ ብዙ ያልተለመደና ያልተዋሀደ ነበር። ያም ሀኖ ከፈረንሳይ አብዮት አንስቶ እስከ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በዘለቀው ጊዜ ውስጥ ፈረንሳይን በየተራ ያስተዳድሩ የነበሩ መሪዎች ፈረንሳያዊ ዜግነትንና ሀገራዊ አንድነትን የመገንባት አስፈላጊነቱን በመረዳት ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ ብዙ ጥረቶችን አድርገው በሂደት ጠንካራ ብሄራዊ አንድነትን ለመፍጠር ችለዋል። ጣልያንም ተመሳሳይ በሆነ የብሄረ መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያለፈች ሀገር ነች። እ.አ.አ በ1860 የጣልያን ሀገራዊ ውህደት ቀንደኛ አራማጅ እና ለተዋሀደችው ጣልያን መመስረት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው Massimo d’Azeglio የሚባለው ጣልያናዊ በውህደቱ ማግስት “….አሁን ጣልያንን ገንብተናል። የቀረን ነገር ጣልያናዊ ዜግነትን መገንባት /መፍጠር/ ነው” ብሎ እንደተናገረ ይጠቀሳል። በተጨማሪም በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ጣልያንና ፈረንሳይን ይመሩ የነበሩ መሪዎች የህዝቦች አንድነትና የጋራ ትስስርን ሊፈጥሩ የሚችሉ በርካታ ፖሊሲዎችን ቀርጸው ተግባራዊ በማድረግ ጠንካራ ብሄራዊ አንድነትን ለማጎልበት ጥረት አድርገዋል። ለዚህ ደግሞ በዜጎች ላይ የአስገዳጅነት ባህሪ ካላቸው የትምህርት ፖሊሲዎች እስከ የጋራ ቋንቋ አጠቃቀም፣ ከብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት እስከ መሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ… ወዘተ ያሉ ሀገራዊ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን ስራ ላይ አውለዋል። በዚህም እነዚህና ሌሎች በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በተነጻጻሪነት ጠንካራ መሰረት ያለው አንድነትና የህዝቦች ውህደትን መፍጠር ችለዋል። ህዝቡም የባለቤትነትና የእኔነት ስሜትን፣ የጋራ ሀገራዊ ራእይና ስነልቦና እንዲኖረው አስችሎታል። ይህ ደግሞ ሀገሮቹ ሰላማዊና የተረጋጋ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መደላደል እንዲኖራቸው አድርጓል። ይህ የምር በታሰበባቸው አስፈላጊ ለውጦችና ማሻሻያዎች የታጀበ የተከታታይ አመታት ስራ ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ማለት ግን በዴሞክራሲና በእድገት ገፍተዋል የሚባሉት የአውሮፓ ሀገራት የብሄረ መንግስት ግንባታ ሂደታቸው አልጋ በአልጋ እና ያለቀ ነገር ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አሁንም ቢሆን በፈታኝ የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ እያለፉ መሆኑን እንረዳለን። በአንዳንዶቹ ሀገራትም ሂደቱ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታን ፈተና ላይ የሚጥልበት ገጽታ ያለው ነው። ለዚህም የክውቤኮች ንቅናቄ በካናዳ፣ የባስክ ትግል በስፔን፣ የእስኮትላንዳውያንን የራስን መንግስት የማቋቋም ጥያቄ በዩናይትድ ኪንግደም መጥቀስ ይቻላል። ይህ ሁሉ ሁኔታ የሚያሳየን የብሄረ መንግስት ግንባታ ሂደት በተወሰነ ጊዜያት ውስጥ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ ነገር ሳይሆን፣ በማያቋርጥና በተደማሪ ተግባሮች፣ በስምምነትና ውህደት፣ እንዲሁም በአስፈላጊ ለውጦች እየተገነባ የሚሄድ ረጅም ታሪካዊ ሂደት እንደሆነ ነው። በዚህ እውነታ መሰረት የኢትዮጵያን ሁኔታ ብንመለከተው የኢትዮጵያ የብሄረ መንግስት ግንባታ ገና ተጠናክሮ የወጣና የተገነባ እንዳልሆነ፣ ሁሌ ተጀምሮ ዳር የማይደርስ መሆኑን ብዙ ምሁራን ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ ይደመጣል። ይህን ሀሳብ የበለጠ የሚያጠናክረው ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ብሄርንና አካባቢያዊ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና የአለመግባባት ሁኔታዎች በተደጋጋሚ መታየታቸውና ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ ብሄራዊ አንድነት ስጋት መደቀኑ ነው። ለእነዚህ ግጭቶችና አለመግባባቶች ዋነኛው መንስኤ ለብሄረሰባዊ ማንነትና ክልላዊነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለብሄራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ማንነትን በተመለከተ በበቂ ሁኔታ አለመሰራቱ፣ ፌዴራሊዝሙ የሚጠይቀውን ተግባር በሚፈለገው ደረጃ አለመተግበር፣ እንዲሁም ወደዚሁ አቅጣጫ የሚወስዱ ተግባራትን ከመፈጸም አኳያ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ መሆኑ በርካታ ምሁራን ይገልጻሉ። ይህ ሀሳብ ሰሞኑን በቢሾፍቱ “አገር ግንባታ በኢትዮጵያ-ለውጥ በቀጣይነት (Nation Building in Ethiopia: Change in Continuity) በሚል ርእስ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ በስፋት ተንጸባርቋል። በዕለቱ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ «Revisiting the legacy of the Ethiopian student movement on the national question» በሚል ርእስ የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ሲሆን፣ ፕሮፌሰር መድሀኔ ታደሰ ደግሞ «The role of history and /or narratives in nation building» በሚል ርእስ የውይይት ሀሳብ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሸ «Organizing education in Ethiopia for nation building» በሚል ርእስ እንዲሁ የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ሲሆን ፣ ዶክተር ቴዎድሮስ ሀይለ ማርያምም ደግሞ «State and nation in Ethiopia: The past and the future» በሚል ርእስ የመወያያ ሀሳብ አቅርበው ጥልቅ ውይይቶች ተካሂደዋል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ የቀረቡ ጥናታዊ ስራዎች የተሳታፊውን ቀልብ በይበልጥ የሳቡና ሞቅ ያለ ውይይትን የጋበዙ ነበሩ። በሲምፖዚየሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንዳሉት የአገር ግንባታ ሂደት ከታሪክ አንጻር ግጭትና ኃይል የበዛበት ሆኖ ይታያል። በዚህ ምክንያት ሂደቱ ብዙ ውጣ ውረድና ወድቆ መነሳት የሚፈራረቅበት የእሽክርክሪት ጉዞ ነው ይላሉ። ከዚህ አንጻር “ኢትዮጵያ በግዛቱ ውስጥ የታቀፉትን ህዝቦች ወደ አንድ ማህበረሰባዊ ቁመና በበቂ ማስተሳሰሪያዎች ለማቆራኘት ስትጥር የቆየች ሀገር ብትሆንም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመንግሥትነት ታሪክ፣ ወግና ልምድ ስለነበረ መንግስታቶቿ መዋቅራዊ ቁጥጥራቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የረዳቸውን ያህል የሂደቱ ባህርይና ውጤት በራሱ ብዙ ማህበርሰባዊ ቅራኔዎችን እየፈጠረም መጥቷል” ሲሉ ያብራራሉ። “እነዚሀ ቅራኔዎች የኢትዮጵያን ህልውና፣ ትንሳኤ፣ ቀጣይነትና ግሰጋሴ ሲፈታተኑ የምናያቸው በዚህ ምክንት ነው” ሲሉም ይገልጻሉ። በመሆኑም “ኢትዮጵያ እንደ አገርና ህዝብ ለረዥም ጊዜ የሚያስቀጥላት፣ በየጊዜውና በየምዕራፉ የሚጠየቁ አስፈላጊ ለውጦችና መሽጋሸጎች እያደረገችና ራሷን እያዘመነችም ግን ሂደቱ ወደፊትና ወደ መጨመር መሆኑ ሳይቋረጥ የግስጋሴ ጉዞዋ ግን አስተማማኝ ዋስትና እያገኘ የሚሄድበት የአገር ግንባታ ቀመር መለየትና መንደፍ ይኖርባታል” ሲሉ በአጽንኦት ተናገረዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ አገላለጽ ይህ የሚነደፈው ቀመር በህዝቦቿም ሆነ በልሂቆቿ መካከል ያለውን የታሪክና የጥቅም ግጭቶች ወይም ልዩነቶች እያጠፋ፤ ስምምነትና ዉህደት እያሰፋና እየገነባ የሚሄድ፣ የህዝቦች ወይም የቡድኖች ወይም የዜጎች ቅሬታና ብሶት እየቀነሰ ሄዶ ወደ አንድ የሚመጋገብ እንጂ የማይጋጭ ህብረተሳባዊ ራእይና ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት የሚወስድ ፍኖተ-ቀመር እንዲሆን ያስፈልጋል። የዚያ ዓይነት አካሄድ ቀጣይነትን እያረጋገጠ አስፈላጊ ለውጦችንም ማስተናገድ የሚችል መሆን አለበት። “የኢትዮጵያን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ማስተሳሰር የሚቻለው፣ አንድም ያለፈውን የኢትዮጵያዊነት አኩሪ ታሪክ፣ እንዲሁም መከራ፣ አሊያም የመጻኢ ጥሩ ዕድልና ተስፋ ተጋሪነት ስሜት አዋህዶ የተመጠነ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው” የሚሉት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት፤ “የዚህ ዓይነት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በምልአት የሚያካትትና እና በብቃት የሚያሳትፍ ለሁሉም ዓይነት አገራዊ ግንባታ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ምሰሶዎችና ትውፊቶች ዕውቅና የሚሰጥ የጉዞ አቅጣጫ መንደፍ ይቻላል ብቻ ሳይሆን ይገባልም” ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ዻዻሳት ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሀነ እየሱስ ሱራፌል «Moral and social foundations for Ethiopian Nation Building» በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ “ኢትዮጵያዊ አንድነት ተነቃንቆ ይሆናል እንጂ ህዝቡ አሁንም ለኢትዮጵያዊ አንድነት መሰረት የሚሆኑና መእስዋትነት እስከመክፈል የሚያደርሱ ሞራላዊና ማህበራዊ እሴቶች በብዛት አሉት” ይላሉ። እንደ እርሳቸው ሃሳብ የኢትዮጵያዊነት ሞራላዊና ማህበራዊ እሴቶች ዘላቂነታቸውና ጥልቀታቸው የሰፋ ነው። እነዚህ እሴቶች ሰብአዊነትን፣ ሀቅን፣ ፍትሀዊነትን፣ መቻቻልን እና የመረዳዳትን ባህል ያቀፉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለሀገር ግንባታ እንደ ምሶሶ እና እንደ መሰረት የሚያገለግሉ ናቸው ይላሉ ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሀነ እየሱስ። “መተባበር ቀንሶ፣ መናናቅና ጥላቻ ነግሶ በዘርና በጎሳ በመከፋፈል የታየው ሁኔታ አሳዛኝና አሳፋሪ ነገር ነው፤ይህ በእሳት እንደመጫወት ይቆጠራል”ይላሉ መንፈሳዊ መሪው። አቡነ ብርሀነ እየሱስ በንግግራቸው ላይ “የተጀመሩት የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይገቱና የሀገሪቱ ነጻነት እንዳይደፈር እነዚህ ሞራላዊ እሴቶችን ማሳደግ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ የችግሮችን መንሴ ማጥናት ያስፈልጋል። አለበዚያ ሁኔታው ለጊዜው የተረጋጋ መስሎ ቢታይም ቀስ ብሎ መፈንዳቱ አይቀርም” ይላሉ። በተጨማሪም ስለ ሀገር ግንባታና ስለ ሰላም አስፈላጊነት በየትምህርት ቤቱና በየኮሌጁ መሰበክ ይኖርበታል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል። አንድነት ያለብዝሀነት፣ ብዝሀነት ያለ አንድነት ትርጉም እንደማይሰጥ የሚያስረዱት የሀይማኖት መሪው፣ አንድነትና ተስፋ ሲነግሱ ህይወት ትርጉም እንደሚኖረው ይገልጻሉ። ይህ ግብ እንዲሳካ ደግሞ መንግስት፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። «Federalism: An Alternative for Nation Building in Ethiopia» በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማእከል ሊቀመንበር እና የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር አሰፋ ፍሰሃ በበኩላቸው የብሄረ መንግስት ግንባታ (ኔሽን ስቴት) አንድ አገር አንድ ሕዝብ በሚለው አስተሳሰብ ለበርካታ ዓመታት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ ብዙ ውጤት አላመጣም። ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተዘረጋው የፌዴራል ስርአትም ይኸው የብሄረ መንግስት /ኔሽን ስቴት/ ግንባታ እየተሞከረ ይገኛል ይላሉ። ይሁንና ከ1983 ወዲህ በቋንቋና ብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተውን የፌዴራል ሥርዓትን መዘርጋት ተከትሎ የተመዘገቡ ብዙ ስኬቶች እንዳሉ ሆኖ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም ዶክተር ፍሰሀ ያነሳሉ። ምሁሩ እንደሚሉት የሀገር ግንባታ ህዝብ ላይ የሚሰራ ስራ ከመሆኑ ጎን ለጎን ተቋማትና የመንግስት መዋቅሮች ላይ፣ ሲቪል ሰርቪሱ ላይ፣ የጸጥታና ህግ አስከባሪ አካላት…ወዘተ ላይ የሚሰራ ስራ ነው። ይሁንና ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት እነዚህንና መሰል መንግስታዊ ተቋማትን/መዋቅሮችን/ ለሀገር ግንባታው በሚበጅ መልኩ ጥቅም ላይ ከማዋል አኳያ መንግስት የቤት ስራውን እንዳልሰራ ይናገራሉ። ሁሉን ያቀፈ፣ የተረጋጋና ሰላማዊ ህብረተሰብ መፍጠር ይቻላል ወይ? የሚለው ዋናው ጥያቄ መሆኑን ያነሱት ዶክተር አሰፋ፤ ጎልተው ከሚታዩ ክፍተቶች አኳያ የሀገር ግንባታው ሂደት በመንግስታዊ መዋቅሮች፣ በፖሊሲና የህግ ማእቀፎች ዙሪያ የማስተካከያ ስራ (ተሀድሶ) እንደሚያስፈልገው ይገልጻሉ። አክለውም የምእራባዊያን ሀገራት እድገት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የሀገር ግንባታ ሂደታቸው ላይ የሚጠየቁ አስፈላጊ ለውጦችና መሸጋሸጎችን በየወቅቱ በማደረጋቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ዶክተር አሰፋ እንደሚሉት ባሁኑ ወቅት የሀገር አንድነትን የሚፈታተኑ ችግሮች እንዳሉ ባይካድም የችግሩ ምንጭ የፌዴራል ስርአቱ ሳይሆን ትግበራው ነው። በመሆኑም “በወደፊቱ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ጨለምተኛ መሆን የለብንም” ይላሉ። “ከዚህ ይልቅ የሀገር ግንባታ ሂደት የማያቋርጥ ቀጣይ ስራ እንደመሆኑ መጠን ለዚህ አስፈላጊ የሆነ ተቋማትን የማጠናከርና አዳዲስ ተቋማትን የመገንባት ስራ ወሳኝ ነው” በማለት ያስረዳሉ። ከዚህ ጎን ለጎንም “የጎደሉትን ነገሮች እየሞሉና ህዝብ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ተገቢና ፍትሀዊ ምላሽ እየሰጡ መጓዝ ለብሄረ መንግስት ግንባታው ይረዳል” ይላሉ። ለዚህም የአሀኑ አዲስ አመረር በህዝቡ መካከል የእኔነትና የባለቤትነት ስሜት እንዲዘራ በማድረግ “የኔ ሀገር፣ የኔ ሰንደቅ አላማ፣ የኔ መንግስት፣ የኔ መሪ...” የሚል አስተሳሰብ በውስጡ የሰረጸና የተዋሀደ ህዝብ እንዲገነባ መስራት ብዙ ይጠበቅበታል በማለት ያስረዳሉ። አንድ የሆነና የተዋሀደ ህዝብ ሲባል ግን ለብዝሀነት ቦታ ሳይሰጥ በቀድሞ ስርአት “ኢትዮጵያ ትቅደም” ሲባል እንደነበረው አነጋገር አንድ ወጥ ወይም «ዩኒፎርም» የሆነ ኢትዮጵያዊነት ማለት እንዳልሆነ ዶክተር ፍሰሃ የካርዲናል አቡነ ብርሀነ እየሱስን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በግልባጩም አንዳንድ ዜጎች ኢትዮጵያዊ ነኝ ብለው በዜግነታቸው ከመኩራት ይልቅ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግሬ ማለትን እንደሚያስቀድሙ በማብራራት፣ እነዚህ ልዩነቶች የሀገር አንድነትንና ኢትዮጵያዊነት ማንነትን በማያደናቅፍ መንገድ በፖሊሲ ጭምር በማስደገፍ ህብረተሰቡ እንዲረዳቸው ትርጉማቸውን ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ባሁኑ ወቅት የህዝቡን ትስስሮች የሚያጠናክሩ አንዳንድ ጥረቶች እንዳሉና ይህም የሚበረታታ ጥሩ ጅማሬ መሆኑን የሚገልጹት ዶክተሩ፣ ነገር ግን አንዱ ህዝብ የሌላውን ህዝብ ማንነት፣ ባህል እና ሌሎች የአኗኗር መስተጋብሮች እንዲያውቅና እንዲያከብር ከማድረግ አኳያ የአፈጻጸም ጉድለቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ። “በመሆኑም እነዚህን ጉድለቶች ለመሻገርና ሁሉንም ያቀፈ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ፈጥረን ነገ የተሻለች ሀገር እንዲኖረን የሚያስችለንን አቅጣጫ መከተል ይጠበቅብናል” ሲሉም ነው ያብራሩት። የመኢሶን መስራቾች ከነበሩት መካከል አንዱና «በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ» መጽሀፍ ደራሲ አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በበኩላቸው «ለኢትዮጵያ ብሄረ-መንግስት ግንባታ አንዳንድ ሀሳቦች» በሚል ርእስ የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህ ጽሁፋቸው አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርአት በተወሰነ ደረጃ በሀገሪቱ ለሰፈነው ሰላም፣ የዴሞክራሲ ጅማሬዎችና ለተመዘገቡ የልማት ውጤቶች አስተዋጽኦ አበርክቷል ይላሉ። ይሁንና በዚሁ መጠን ህገ መንግስቱን በትክክል ስራ ላይ አለማዋል፣ የህግ የበላይነት አለመከበር፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ…ወዘተ የመሳሰሉት ተገዳሮቶች የሀገሪቱን ሀልውናና አንድነት የሚፈታቱኑ አደጋዎችን መፍጠራቸውና ከዚህ ባልተናነሰም በመንግስት ውስጥ ያለው የሙስናና «የእከክልኝ ልከክልህ» አሰራር በሀገር ህልውና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። “እነዚህ ችግሮች ሊፈጠሩ የቻሉት የብሔር ብሔረሰብ መብት ስለተከበረ ወይንም የፌዴራል ስርአት ስለተዘረጋ አይደለም” የሚሉት እኝህ ፖለቲከኛ “የችግሮቹ ምንጭ የፌዴራል ስርአቱን ለመተግበር የተኬደባቸው መንገዶች ናቸው” በማለት የዶክተር ፍሰሀን ሀሳብ በመደገፍ ያብራራሉ። አክለውም “አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት በህገ መንግስት ደረጃ እንደ ራእይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ወደዚሁ አቅጣጫ የሚወስደን በርካታ ፖለቲካዊ ስራዎች ባለመሰራታቸው ሀገሪቷ ዛሬ የምትገኝበት ፈተና ውስጥ ልትገባ ችላለች” ይላሉ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው ገለጻ የብሄረ መንግስት ግንባታ ከቡድን ማንነት ጋር የተቆራኙ ስሜቶች የሚነሱበትና የሚራመዱበት በፈተና የታጀበ ሂደት ነው። በመሆኑም ለመንግስት የሚቀርቡ የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲና የማንነት ጥያቄዎች የጋራ ስትራቴጂ ላይ በተመሰረተ የድርድርና የውይይት ሂደት የህዝቡን ፍላጎት ሊያረካ የሚችል ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም “የሀገር ግንባታ ሂደት የአንድ ፓርቲ ወይም የልሂቃን ስራና ሀላፊነት ብቻ አይደለም፤ የህዝቡም ስራ ነው” የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፤ እስከታች ወርዶ ህዝቡን ያሳተፈ፣ የዴሞክራሲ ሰርአት መዘርጋትና ማጠናከር፣ እንዲሁም በነጻነት እንዲቆጣጠረው ማደረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። “አሁን በሀገሪቱ የተደቀነውን ፈታኝ ሁኔታ አቅልሎ ማየት ባይቻልም፣ የማይፈታ ግን አይደለም” የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ “ፈተናው መልካም እድሎችንም፣ ስጋቶችንም አብሮ ያቀፈ ነው” በማለት ያብራራሉ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው ገለጻ በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረው ሀገራዊ ፈታኝ ሁኔታ ገዥው ፓርቲና መንግስትን ከተኙበት እንዲነቁ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም ተሀድሶና ጥልቅ ተሀድሶ በሚሉ መፈክሮች ስር እራሱን እንዲፈትሽና እንዲያጤን አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ “የት ላይ ነን? ወዴት እየሄድን ነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች እንዲጠይቅና ህይወቱን የሚነኩ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታዎችን በንቃት እንዲከታተል ጠቅሟል ነው ያሉት። “በዚህ የተሀድሶ ንቅናቄ መንግስት ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ጥያቄዎቹን ያገናዘበ ፈጣንና ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ የተጋረጠውን ፈተና የማለፍ መልካም እድል አለ” የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ “ለፈተናዎቹና ከህዝቡ ለሚደመጡ ጥያቄዎች መሰረታዊ መፍትሄና ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ አሁን ከተገኘው አንጻራዊ ፋታ ተመልሰን ወደ ግርግርና ብጥብጥ የማንገባበት ምንም ዋስትና የለም በማለት” ያስገነዝባሉ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው አነጋገር ኢትዮጵውያን አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና የመተባበር አኩሪ ባህልና ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። በመሆኑም ህዝቡ፣ ምሁራንና የታሪክ ሰዎች በእነዚህ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የጋራ እሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ሀገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ በአጽንኦት ይገልፃሉ። “ባለፈ የታሪክ ጠባሳ ላይ ተጠምዶ እርስ በእርስ መጎዳዳትና መጠላላት ሀገራዊ አንድነትን የሚሸረሽርና ምንም ፋይዳ የሌለው ነው” የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው “ ምሁራን የኋላ የጋራ ታሪኮችን ፈትፍተው በመጻፍ ህዝቡ እንዲቀራረብና ኢትየጵያዊ አንድነቱ እንዲያጠናከክር ማድረግ ይገባቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል። በአጠቃላይ “እነዚህን የሀገራዊ መግባባትና የብሄራዊ አንድነት ራዕዮችን ለማሳካት ከሀገሪቱ መሪዎች ጀምሮ በየተዋረዱ ያሉ አመራሮች፣ መምህራን፣ ምሁራን ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች… ወዘተ ህዝቡን በተገቢው ሁኔታ ሲያገለግሉ ራዕዩ ውጤታማ ይሆናል” ይላሉ አቶ አንዳርጋቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ካለፉ ስህተቶች በመማር ተጨባጭነት ያላቸውና በእውነታ ላይ የተመሰረቱ ራዕዮችን የሚያስቀምጡ፣ አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ፣ እንዲሁም እንዲያብብ ለሚፈለገው የሀገር አንድነት ግንባታ የሚመጥኑ እውቀት፣ ብስለትና ትጋት ያላቸው አመራሮች ለኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ባሁኑ ወቅት ያስፈልጋታል” የሚሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ “የዛሬ አመራሮች ታሪክ ጥሩ ግብዣ አድረጎላቸዋል፤ ይሄንን ግብዣ ማባከን አያስፈልግም” በማለት ነው ሀሳባቸውን የቋጩት።