ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌትን ማጠናቀቋ በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ መድርኮች የመደራደር አቅሟን ያጎለብታል-ምሁራን

ሐዋሳ ሐምሌ 14/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌትን በስኬት ማጠናቀቋ በቀጠናዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች የመደራደር አቅሟን ያጎለብታል ሲሉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን አስታወቁ።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሀይድሮሊክስና ውሃ ሃብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሞልቶት ዘውዴ ኢዜአ እንዳሉት ኢትዮጵያ በውስጥና ውጫዊ ጫናዎች ሳትበገር የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌትን ማጠናቀቋ ስኬታማነትን ያጎናጽፋታል።

የግድቡ የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን የሞራል ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል ።

በተለይ በዲፕሎማሲ ረገድ መንግስት እውነታን ለማስረዳት በፀጥታው ምክር ቤት ያደረገውተጋድሎየጎላ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት እውነታውን እያወቀ ለግብጽና ሱዳን ሲል በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ አጀንዳ ይዞ ቢሰየምም ኢትዮጵያ በወኪሎቿ አማካኝነት ባሳየችው ብቃት አስደማሚ ውጤት ማስመዝገቧን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ተግዳሮቶችን በመቋቋም የህዳሴ ግድቡን 2ኛ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋ ከዚህ በኃላ በሚኖሩ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የመደራደር አቅማን እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያ በዜጎቿ የትኛውንም ተፅዕኖ መሻገር እንደምትችል አሳይታለች" ያሉት ዶክተር ሞልቶት "ጠላቶቻችን እኛን ለመጉዳት እኛኑ ስለሚጠቀሙ በቀጣይ በር የሚከፍቱ ልዩነቶችን በመመካር ማክሰም ይገባል" ሲሉም  ጠቁመዋል።

"ኢትዮጵያ ከፍ እያለችና ተደማጭ እየሆነች በመምጣቷ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የገጠማቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ የሚያደርጉት ተጽዕኖ የሚቆም አይደለም" ያሉት ዶክተር ሞልቶት ዕውነታውን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የማስረዳቱ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል።

የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን  አቅማቸውን ማጠናከርና ከመንግስት አካላት የሚሰጡት መግለጫዎችን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ተገዳዳሪዎቻችን ሊሰሙት በሚችሏቸው ቋንቋዎች በተደራጀ አግባብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ሃብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቴዎድሮስ አሰፋ በበኩላቸው ዜጎችና መንግስት በግድቡ ዙሪያ የሀገርን ጥቅም ለማስከበር ያደረጉት የተቀናጀ ጥረት ለውጤት መብቃቱን ጠቅሰዋል።

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እየተገኘ ያለው ውጤት የኢትዮጵያን  የመልማት ፍላጎትና መብት ከማስከበር ባለፈ በቀጣይ በሚኖሩ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ መጥፎ ጠባሳ ሊያሳድሩ የሚችሉ ተፅዕኖዎችን ለመቀልበስ የሚያስችሉ መሆኑን አስረድተዋል።

የግድቡ ግንባታ ፍጻሜ እስከያገኝ ድረስ ምሁራንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ትንታኔዎችን በማቅረብ ዕውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስጨበጥ የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እንደ ዶክተር ቴዎድሮስ ገለጻ በአባይ ውሃ ዙሪያ የዓለም ማህበረሰብ ብዥታ ውስጥ እንዲገባ ያደረጉ ለረጅም ዓመታት ሲነገሩ የቆዩ ሁለት የተሳሳቱ ትርክቶች አሉ።

የግብጽንና የሱዳንን የውሃ ሃብት አሳንሶ በማሳየት፣ ከአባይ በቀር ውሃ የለንም በማለት ኢትዮጽያ በርካታ የውሃ ሃብት ስላላት አባይን አትንካብን የሚሉ የተሳሳቱ ትርክቶች መኖራቸውን አብራርተዋል።

"በሀገራቱ አባይ ለዘመናት በመፍሰስ  የተከማቸና ወደ ፊት ያለ ስጋት ሊጠቀሙበት የሚችል የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት እንዳላቸው እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደማንኛውም ሃገር የውሃ እጥረት ያለባት ሃገር መሆኗን ለዓለም በማሳወቅ ስህተቶችን ማረም ይገባናል" ብለዋል።

"የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው" ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ ግንባታው በምንም ዓይነት ሁኔታ ሳይደናቀፍ ዕውን ሆኖ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል  ሁሉም ዜጋ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍና አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም