ቀጥታ፡

ሕዳሴ ግድብ የደራሲያንን የብዕር አተያይ ቀይሯል

ሐምሌ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር የዓባይ ዘመን ብዕሮች ከሃዘን፣ ቁጭትና እንጉርጉሮ ተላቆ በተስፋ፣ በጥቅም፣ በሕብረት፣ በአንድነት ጉዳዮች መተካቱን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ይገልጻል።

የዓባይ ወንዝ በስነ ቃልም ሆነ በስነ ጽሁፍ መስክ ሰፊ ቦታ ይዟል።

ዓባይ ውሃ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተፋሰሱ አገራት ከእምነትም ከማኅበረሰቡ ባሕላዊና ትውፊታዊ ኪነት ተሻግሮ የዘመናዊ ኪነ ጥበቡን ቀልብ ገዝቶ ኖሯል።

የኢትዮጵያ ከያኒያን የተመስጦ ጥጋቸውን በወንዙ ላይ አድርገው ሙዚቀኞች አዚመዋል፤ ባለቅኔዎች ተቀኝተዋል፤ ሠዓሊያን በሸራቸው ተራቅቀዋል።

የደራሲያን ብዕራቸው በዓባይ ተፋሰስ ላይ ተንከራቷል።

ለአብነትም ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ አቤ ጉበኛ፣ አያልነህ ሙላቱ፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ኃይሉ ገብረ ዮሃንስ (ገሞራው)፣ ሙሉጌታ ተስፋዬና ኮሎኔል ሞገስ ሀብቱ በዓባይ ላይ ከተቀኙ ባለቅኔዎች መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ አዳሙ “የቅድመ 2003 ዓ.ም የዓባይ ግጥሞች ይዘት በቁጭት፣ በምኞት፣ በሽሙጥ፣ በፀፀት፣ በእርግማን፣ በቁጣና ተማጽኖ ላይ ያተኮሩ ነበሩ” ይላል።

የግድቡ መጀመር የገጣሚያን የስነ ግጥም ይዘት እንዲለወጥና የዓባይ ግጥሞችና ገጣሚያን ብዛትም እንዲጨምር ማድረጉንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ከግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር አንጋፋና ወጣት ደራሲያን የተሳተፉበት ሁለት የጽሁፍ ስራዎች መታተማቸውንም ጠቅሷል።

ዓባይ ነባርና አዳዲስ ገጣሚያንን ማነሳሳቱን፣ የደራሲያን ስራዎች ደግሞ ማኅበረሰቡን ለንቅናቄ በማነሳሳት ትልቅ ኪነ ጥበባዊ አበርክቶ እንደነበረው ተናግሯል።

ከሰሞኑ የተጠናቀቀው ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌትም የደራሲያንን ምኞትና ተስፋ ለፍሬ እንዲበቃ ቀጣይነት ያለው እርምጃ መሆኑን ገልጿል።

“የግድቡ ውሃ ሙሌት የኢትዮጵያ የደስታና የሀዘን እንባ ነው” የሚለው አቶ አበረ፤ “ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች እያሉ ኢትዮጵያ በስኬት መሙላቷ የደስታ እንባ ነው” ብሏል።

“በመከራ ውስጥ መሆኗ ደግሞ የሀዘን እንባ ያደርገዋል” ሲል ተናግሯል።

ደራሲና ጋዜጠኛ አበረ ግጥሞቹ 'አባይ የሁሉም የጋራ ሀብት ነው' በሚል ሃቅ ላይ የተቃኙ እንደሆኑ ገልጾ፤ የዓባይ ጉዳይ መልከ ብዙ ፖለቲካዊ ክሮችን የሚበጥስ እንደሆነ አብራርቷል።

“ዓባይ በስልጣኔ፣ በሃብት፣ በኩራት፣ በውበት ምንጭነትና በአገር ቅርስነት በቁጭት ሲወሳ ቢኖርም ዛሬ ደግሞ የተበላሸውን የፖለቲካ ስርዓት የሚጠግን፣ ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ያሰባሰበ፣ ሕብረታቸውን የሚያጸና ነው” ብሏል።

የግድቡ የሚዲያና ኪነ ጥበብ ስራዎች ወቅት እየጠበቁ ሳይሆን በተከታታይ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

የዓባይ ጉዳይ በትምህርት ስርዓቱ ተካቶ ትውልድ ሊማርበት እንደሚገባም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም