ቀጥታ፡

የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ ህዝብና መንግሥት ድጋፋቸውን ያጠናክራሉ .. ርዕስ መሰተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 14/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰፊውን ህዝብ ከጨለማ የሚያወጣ በመሆኑ ቀሪው ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ የክልሉ ህብረተሰብና መንግሥት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የሲዳማ ክልል ርዕስ መሰተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ከሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የህዳሴ ግድብ  ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን በመደገፍና የአሸባሪውን ሕወሓት  ጥቃት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ አካሂደዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያዊያን ከልጆቻቸው ጉሮሮ  ጭምር እየነጠቁ ግድቡን ለመገንባት ተረባርበዋል።

ሆኖም በሂደቱ አያሌ ፈተናዎች መግጠሙን ጠቅሰው በተለይ ስልጣን ተቆናጥጦ የነበረው የህወሓት ጁንታ በግድቡ ስም ገንዘብ እያሰባሰበ ከፍተኛ ዘረፋ ማካሄዱን አመልክተዋል።

በዚህ ሁሉ ዜጎች ተስፋ ሳይቆርጡ ገንዘባቸውን አውጥተው ግድቡ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያዊያን ህልም እንዲሳካ የለውጡ መንግሥት በግድቡ ዙሪያ የነበረውን ችግር  በማጤንና ቆራጥ እርምጃ በመውስድና ከውጭ የሚደርስበትን ጫና በመቋቋሙ ግድቡ ውሃ እንዲይዝና ወደ ምርት እንዲሸጋገር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።  

ይህም የለውጡ ከፍተኛ ተምሳሌትና ትሩፋት አድርጎ መውሰድ እንደሚቻል ርዕሰ  መስተዳድሩ አውስተዋል።

ግድቡ  ሰፊውን ህዝብ ከጨለማ የሚያወጣ በመሆኑ ቀሪው ግንባታ ለፍጻሜ እንዲበቃ  የክልሉ ህብረተሰብና  መንግሥት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉበትም አስታውቀዋል።

ጁንታው  "ከጎረቤት ሀገራት ተልዕኮ ወስዶ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል  በሰፊ  ከመንቀሳቀስ አልፎ ዛሬ ላይ በሀገሪቱ ላይ ጥቃት ማድረሱ" በቃህ  ሊባል  እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ "የአሸባሪው ርዝራዠመልሶ እንዳይበቅል በማድረግ ሠላማችንንና ልማታችንን አስተማማኝ ለማድረግ ከህዝባችን  ጋር ተባብረን እንሰራለን" ብለዋል።

በተለይ የክልሉ ህዝብ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስከበር ሌት ተቀን እየደከመ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲያጎለብትም  ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፤ ግድቡ ድህነትን ለማሸነፍ ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የተካሄደው ሰልፍ ዋና ዓላማ ሀገሪቱን ከልማቷ ማስቆም እንደማይቻል ለወዳጅም  ለጠላትም ለማስገንዘብ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከሰልፉ ተካፋዮች መካከል አቶ ከበደ ባይሶ በሰጡት አስተያየት፤ በግድቡ ሁለተኛው  ዙር የውሃ  ሙሌት መደሰታቸውን ገልጸው ፤ ግንባታው እስኪጠናቀቅ  ድረስ  አስፈላጊውን  ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ለገሠ ነጋሽ የተባሉ የሰልፉ ተሳታፊ በበኩላቸው፤ ግድቡ ለሀገሪቱ ምጣኔ  ሀብታዊ  እድገት ከሚያስገኘው ጥቅም ባሻገር  ዜጎችን በአንድነት በማስተሳሰር መሠረት የጣለ  በመሆኑ እስከፍጻሜው ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።  

ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና  የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ  መሆናቸውን  ለመግለጽ በሰልፉ  መካፈላቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ፀዳለ ጌታቸው ናቸው።

የሰልፉ ተካፋዮች ከማለዳው 12 ሰዓት  ጀምሮ  በሀዋሳ ሚሊኒየም አደባባይ  በመገኘት  ለግድቡ ድጋፋቸውን በመግለጽ፤ የአሸባሪውን ህወሓት ጥቃት ያወገዙ ሲሆን  ለሀገር  መከላከያ ያላቸውን አጋርነት በሰጡት አስተያየትና ባሰሙት መፈክር አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም