ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የትውልዱን የአሸናፊነት ስነ ልቦ ገንብቷል- የባህር ዳር ነዋሪዎች

ባህር ዳር ሐምሌ 13/2013 ( ኢዜአ) መላ ኢትዮጵያዊያን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የትውልዱን የአሸናፊነት ስነ ልቦና መልሶ የገነባ ነው ሲሉ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢዜአ የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ ብስራትን አስመልከቶ ከባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል።

የከተማው ነዋሪ አቶ ደሳለኝ ገላው እንደገለጹት  ኢትዮጵያ የገጠሟትን ተደራራቢ  ፈተናዎች ተቋቁማ በዜጎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በድል ማጠናቀቋ የተለየ ደስታ ፈጥሯል።

"የግድቡ ግንባታ አሁን ላለበት ደረጃ  የደረሰው የኢትዮጵያ ህዝብ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከጉሊት ነጋዴ እስከ ባለሃብት በራሱ ገንዘብ፣ ጉልበትና አንጡራ ሃብት የገነባው በመሆኑ  ነው" ብለዋል።

"ግድቡ ኃይል አመንጭቶ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጾ ማድረግ እስኪጀምር የግንባታውን ቀሪ ስራ ለማጠናቀቅ  ድጋፋችንን አጠናክረን  እንቀጥላለን "  ሲሉ  ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ  እንዳትለማና እንዳታድግ የተሰለፉ የውጭና የውስጥ ጠላቶችን በመመከት  የቀደመ አንድነቷን ጠብቃ ድሉን በአሸናፊነት እንድትወጣ  የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን " ብለዋል።

በአስቸጋሪ ወቅት የተገኘው የድል ብስራት የኢትዮጵያዊያንን ጥንካሬና ብልሃት ያሳየ መሆኑን ጠቁመው የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ትውልዱን ለበለጠ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ያነሳሳ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቅርቡ ግብፅና ሱዳን የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ ለፀጥታው  ምክር ቤት ያቀረቡት አቤቱታ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አሸናፊነት መደምደሙ ለስኬቱ አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቅሷል።

"የህዳሴው ግድብ የሚኖረውን አህጉራዊና ቀጠናዊ ጠቀሜታን ለአጋሮች ለማስረዳት አሁንም ዓለማቀፋዊ የዲፕሎማሲ ስራችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል" ብሏል።

"ጠላቶቻችን እንዳንበለፅግ ተባብረው የከፈቱብንን የስነ ልቦና ጦርነት መቀልበስ የምንችለው ሁሉ በየተሰማራንበት የስራ መስክ ጠንክረን መስራት ስንችል ነው" ሲል አመልክቷል ።

ከዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ የ5 ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን አስታውሶ  የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ  መሆኑን  ተናግሯል።

የህዳሴው ግድብ 2ኛው ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ ትውልዱ የአሸናፊት መንፈስ እንዲሰማው ያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

 "በኢትዮጵያዊያን ፀሎት፣ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ አሸንፈን ለድል በቅተናል" ሲሉ በግድቡ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት ደግሞ መቶ አለቃ ተስፋዬ ጫሪ ናቸው።

"አባይ የዘመናት የልማት ህልማችንን የምናሳካበትና ለልጅ ልጆቻችን የሚበቃ አንጡራ የተፈጥሮ ሃብታችን በመሆኑ የግብፅና ሱዳን ሴራን በማክሸፍ ግድቡን ዕውን ከማድረግ የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም " ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የ3 ሺህ ብር ቦንድ  በመግዛት የዜግነት  አሻራቸውን  እንዳሳረፉ ገልጸው የግድቡ ግንባታ  ለፍፃሜ እስኪደርስ  አቅማቸው  የፈቀደውን  ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

ወጣት አድማስ ፀጋ በበኩሉ "የኢትዮጵያዊያንን ድካምና ጥረትን ፈጣሪ አይቶ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት በድል በመጠናቀቁ ተስፋችን ለምልማል"  ሲል ደስታውን ገልጻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም