ድርብ በአል እያከበርን ነው-- በድሬዳዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
ድርብ በአል እያከበርን ነው-- በድሬዳዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች
ድሬዳዋ ሀምሌ 13/ 2013 ( ኢዜአ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የዘንድሮን የአረፋ በአል ድርብ አድርጎታል ሲሉ በድሬዳዋ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።
የህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሃሙሌት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት የእምነቱ ተከታዮች ለግደቡ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለኢዜአ አስታውቀዋል ።
በከተማው ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዛሬ የአረፋ በአልን በመረዳዳት ከማክበር ጎን ለጎን የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በአሉን ድርብ እንዳደረገው ገልጸዋል ።
ከእምነቱ ተከታዮች መካከል አቶ ኢዮብ አደም እንደገለጹት የዘንድሮ የአረፋ በአል የህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ ብስራት በተሰማበት ማግስት መከበሩ ድርብ አድርጎታል።
ሙስሊሙ ህብረተሰብ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ሀገርን ለመናድ የሚደረገውን ማናቸውንም ጥፋት የመቃወምና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
"ያለ ሰላም ምንም ነገር ሊሳካ የማይችል በመሆኑ የሀገር ሰላም በአስተማማኝ መንገድ እንዲረጋገጥና የተጀመሩ ልማቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ድጋፍ አደርጋለሁ" ብለዋል፡፡
"በዓሉን እንደወትሮው ካለኝ ላይ ለተቸገሩ በማካፈል እያከበርኩ ነው፤ የህዳሴ ግድብ 2ተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በድል በተጠናቀቀበት ማግስት መከበሩ በአሉን ድርብ አድርጎታል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሙንተሃ መሐመድ ናቸው።
ወጣት እስክንድር አብዱላሂ በበኩሉ "በዓሉን ስናከብር በሰሜን የሀገራችን ክፍል ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ የተሣተፉትን የሠራዊት አባላት በመደገፍና በፀሎት በማሰብ ሊሆን ይገባል" ብሏል፡፡
"ያለ ሰላም ልማቱ ዳር አይደርስም" ያለው ወጣት እስክንድር የህዳሴ ግድብ የሚፈለገውን ፍሬ እስኪሰጥ ድረስ ወጣቱ በዕውቀቱ ፣ በገንዘቡና በጉልበቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
ሌላው ወጣት ቶፊቅ ማሃዲ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌት በመጠናቀቁ ድርብ በዓል እያከበረ መሆኑን ገልጿል፡፡
"ከ6ተኛ ክፍል ጀምሮ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ ለሶስት አመታት ቦንድ ገዝቻለሁ፤ባለፈው እሁድ የግድቡ ዋንጫ ቀበሌያችን መግባቱን ተከትሎም ተጨማሪ የቦንድ ግዥ ፈጽሜያለሁ" ብሏል፡፡
"የኔና የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ፣ ላብና ዕውቀት ፍሬ እያፈራ መሆኑን በበዓሉ ዋዜማ በህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር ውሀ ሙሌት መጠናቀቅ ብስራት በመስማቴ ደስታዬ ድርብ ነው" ያለው ደግሞ ወጣት ያሲን ጀማል ነው።
ዛሬ የአረፋን በአል "ግድቡ የኔ ነው" የሚል ሃሳብ የተፃፈበት ወረቀት ይዞ ድርብ በአል እያከበረ መሆኑን ገልጿል።
"ግድቡ የኔም የሁላችንም በመሆኑ እስከ መጨረሻው አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጋለሁ " ሲል ተናግሯል።
በውጭ ሀገራት ያሉት ኢትዮጵያዊያን በአረብኛ ቋንቋ በሚታተሙ ጋዜጠኞች ስለግድቡ ትክክለኛ መረጃ ለዓለም ለማሳወቅ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልእክት አስተላልፏል።
"ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነቱን በመጠበቅ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ዳር እንዲደርስና ሰላም እንዲረጋገጥ መትጋት አለበት" ያሉት ደግሞ አቶ መሐመድ ሌይን ናቸው።
ህዝቡ አንድነቱን በመጠበቅ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሴራን ሊከላከል እንደሚገገባ አስገንዝበዋል።
ወጣት ሹክሪያ መሐመድ በበኩሏ የግድቡ ዋንጫ ድሬዳዋ መግባቱ በየደረጃው የሚገኘው ህዝብ ለግድቡ እያሳየ የሚገኘውን ፍቅርና ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክር ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ተናግራለች፡፡
የአረፋን በአል ከህዳሴው ግድብ 2ኛ ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቅ ጋር በጥምረት እያከበርን በመሆኑ ደስታችን ድርብ ነው" ብላለች ወጣት ሹክሪያ መሐመድ።