ህዝበ ሙስሊሙ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርግ የጂንካ ከተማ መስጂድ ኢማም ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርግ የጂንካ ከተማ መስጂድ ኢማም ጠየቁ
ጂንካ፣ ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) የሀገር ኩራትና መለያ አርማ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ ህዝበ ሙስሊሙ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርግ የጂንካ ከተማ መስጂድ ኢማም ሼህ እንድሪስ አህመድ ጠየቁ።
1 ሺህ 442ኛውን የኢድ አል አደሃ አረፋን በዓል በጂንካ ከተማ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በስግደትና ሶላት ስነ-ስርዓት በድምቀት አብበረዋል፤ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ በማበርከት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ሼህ እንድሪስ እንዳሉት፤ የዘንድሮው አረፋ በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በተጠናቀቀ ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል።
ይህ ታላቅ ግድብ የሀገራችን ኩራትና መለያ አርማችን ስለሆነ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ህዝበ ሙስሊሙ ያልተቆጠ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ሀገሩን የሚወድ እና ለሀገሩ ዘብ መቆም እንደሚገባው ጠቁመው ከሌሎች እምነት ተከታይ እህትና ወንድሞቹ ጋርም በፍቅር፣ በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከአረፋ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ የምንማረውም ታዛዥነት ነው ያሉት ሼህ እንዲሪስ ፤ታናናሾች ታላላቆችን መታዘዝ ፤ወጣቶችም የሽማግሌዎችን ምክር መስማት የፈጣሪን ትእዛዝ ማክበር እንደሆነ አስረድተዋል።
የኢድ አል አደሃ በዓልን ህዝበ ሙስሊሙ ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች ስግደትና የሶላት ስነ-ስርዓት ባካሄዱበት መረሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ደጀን ለሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለህዳሴው ግድብ ገንዘብ በማበርከት ድጋፋቸውን በተግባር ገልጸዋል።