ቀጥታ፡

ለሀገር ሰላምና ልማት በአንድነት መቆም ያስፈልጋል ... የጋምቤላ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት

ጋምቤላ፤ ሐምሌ 13/2013(ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ አብሮነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና ልማት በአንድነት ሊቆም እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ።

1ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሃ / አረፋ/ በዓል በጋምቤላ ከተማ በሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ተከብሯል።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ የሱፍ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮው የአረፋ በዓል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በተጠናቀቀበት ወቅት የተከበረ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

በዓሉን ያለው ለሌለው በማካፋልና በመረዳደት በደስታ ማክበር አንዳለበት አመልክተው፤ እንደ ሀገር እያገጠመ ያለውን የሰላም ችግር ለመሻገር ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታይ እህት ወንድሞቹ ጋር ያለውን አንድነት በማጠናከር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በዓል ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት፤ የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዶራር ኮም ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዘንድሮ የአረፋ በዓል የኢትዮጵያ የአንድነት አሻራና የሉዓለዊነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተጠናቀቀበት ማግስት መከበሩ ከንቲባው ተናግረዋል።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ፍፃሜውን እስከያገኝ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጀመረውን ሁለንተዊ ተሳትፎ አጠክሮ እንዲቀጥል አመልክተዋል።

ከእምነቱ ተከታዮች መካከል ሼህ ዛኪር ኢብራሄም በሰጡት አስተያየት፤ የዘንድሮውን የአረፋ በዓል ከታላቁ የህዳሴ ግዳብ የውሃ ሙሌት ጋር በድርብ ደስታ እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየጣሩ ያሉት የውስጥና የውጪ ኃይሎች ለመመከት ሁሉም በሃይማኖትና በቋንቋ ሳይገደብ  ሀገሪቱን ለመታደግ በአንድነት መስራት ይገባናል ብለዋል።

የዘንደሮ ኢድ አል አድሃ /አረፋ/ በዓል ከህዳሴው ግድብ ጋር በማጣመር እንደ ሁለት በዓል  በደስታ እያከበሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሼህ ሙሐመድ ሐሰን ናቸው።

አሁን ላይ በሀገሪቱ እያገጠመ ያለውን ፈተና ለማለፍ ከመንግስትና ጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም