የዘንድሮው ምርጫ ህዝቡ ፓርቲዎችን በያዙት አጀንዳ መለየት መጀመሩን ያሳየ ነው--ዶክተር ዲማ ነገዎ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው ምርጫ ህዝቡ ፓርቲዎችን በያዙት አጀንዳ መለየት መጀመሩን ያሳየ ነው--ዶክተር ዲማ ነገዎ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተፎካካሪ ሆነው በመቅረባቸው ብቻ ሳይሆን ይዘው በቀረቡት አጀንዳ መለየት መጀመሩ 6ኛው አገራዊ ምርጫ አስተምሮን ያለፈ መሆኑን ዶክተር ዲማ ነገዎ ገለጹ።
"6ኛው አገራዊ ምርጫና የባለድርሻ አካላት ሚና" በሚል ርዕስ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ውይይት ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ ከመንግስት አማካሪዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ውይይቱን የመሩት የገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ምክር ቤት አባልና በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ለፓርላማ መቀመጫ በግል ተወዳድረው ያሸነፉት ዶክተር ዲማ ነገዎ እንዳሉት ምርጫው ጠላትም ይሁን ወዳጅ ከጠበቀው በተለየ መልኩ አስተማሪና ታሪካዊ ሆኖ አልፏል።
“ህዝቡ ፓርቲዎችን ባነሱት የተቃዉሞ ድምጽ ብቻ ሳይሆን ይዘው በቀረቡት አጀንዳ መለየት መጀመሩ መልካም ነው” ያሉት ዶክተር ዲማ፤ ሆኖም ግን የፓርቲዎች አቅም አለመመጣጠን ለወደፊቱም ልንደርስበት ካስቀምጥነው ግብ አኳያ ተግዳሮት ሆኖ ሊቀጥል ይችላል ብለዋል።
የመንግስትና የፓርቲ ድርሻ አለመለየትም ለወደፊቱ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
ለውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በዘርፈ ብዙ ጫናዎች መካከል የተካሄደው የዘንድሮው ምርጫ ከብዙዎች ግምት ውጭ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ የባለድርሻዎችን አስተዋይነት ያጎላ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የመራጩን ህዝብ አስተዋይነት፣ ፅናትና ትዕግስት እንዲሁም የምርጫ ቦርዱ ያላሰለሰ ጥረት ሳይጠቀስ እንደማይታለፍ በማውሳት።
ከምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም የመጡት ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በበኩላቸው ከምርጫ ውጤት በላይ ዋናው መነጋገሪያ የነበረው ከምርጫው በፊት የነበሩት ውዥንብሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሁለንተናዊ ውይይት ከምርጫው መቅደም አለበት በሚሉት ድምጾች ጫና መኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ብርሃኑ፤ አገሪቷ በአገረ መንግስት ግንባታ ዙሪያ ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት አንስተዋል።
ሁሉን ያሳተፈ ውይይት ይቅደም ወይስ ምርጫው ተደርጎ በምርጫው ቅቡልነት ያለው መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ይሻላል የሚሉት ሐሳቦች ከክርክሮች መካከል ዋነኛው እንደነበረም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ተጽዕኖ ነጻ እንደነበር ያነሱት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ቀጄላ መርዳሳ ናቸው።
አቶ ቀጄላ ምርጫው የሁሉንም ችግሮች መልስ እንደማይሰጥና አገራዊ ውይይቱ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
ህዝቡ ዋልታ ረገጥነትን፣ የመንግስትን ጉድለት ብቻ እየጠቀሱ መቀስቀስና ያለ አጀንዳ መቅረብንገዎበድምጹ የቀጣበት በተቃራኒው ሰላምና መረጋጋት፣ የህግ የበላይነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የመሳሰሉትን ለተመራጩ መንግስት የቤት ስራ የሰጠበት ምርጫ ሆኖ ማለፉን ተሳታፊዎቹ ተወያይተውበታል።