ህዝበ-ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ-ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) ህዝበ-ሙስሊሙ አንድነቱን በማጠናከር ለአገር ዕድገትና ለሕዳሴው ግድብ ዳር መድረስ እያበረከተ ያለውን አስተዋጾኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
1 ሺህ 442ኛውን የኢድ-አል አደሃ (አረፋ) በዓል ብዛት ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች በተገኘበት በስግደትና በተለያዩ የሃይማኖታዊ ስርዓቶች ዛሬ በድሬዳዋ አስተዳደር በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።
የአስተዳደሩ የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ አብደላ በራሪቲ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ሙስሊሙ ህብረተሰብ በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት፣ የታረዙትን በማልበስና የታመሙትን በመጠየቅ ማክበር ይኖርበታል።
በተለይ በሃይማኖት ከሚከፋፍሉና ሀገርን ለማፍረስ ከሚታትሩ አጥፊዎች በመራቅ ሙስሊሙ ከሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ያለውን ህብረትና አንድነት እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለሀገር ሰላምና አንድነት በመትጋት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።
የድሬዳዋ ኡላማዎች ምክር ቤት ተወካይ ሼህ አሚን ኢብሮ በበኩላቸው፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉ የጋራ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
"ኃይማኖቱ በሚያዘው መሠረት ለበዓሉ ከሚፈጽመው እርድ አንድ ሦስተኛውን ብቻ በመጠቀም ሌላውን ለጎረቤትና ለተቸገሩ በማካፈል የበዓሉን ደስታ ማጋራት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡
"በተለይ የዘንድሮ በዓል የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በተጠናቀቀ ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርጋገዋል" ያሉት ሼህ አሚን፣ ግድቡ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል ድረስ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አንድነቱን በማጠናከር ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
"የውጭ ሚዲያ ነጋ ጠባ ስለ ዓባይ ሲያወራ የእኛ ሚዲያ ደግሞ መቀዛቀዝ ይታይበታል፤ ይህን በማሻሻል ለህዝቡና ለዓለም ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በየጊዜው ማሰራጨት ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል፡፡
በተለይ አሁን ሀገር ካለችበት አጣብቂኝ ወጥታ ወደፊት እንድትራመድ የሁሉም ዜጋ ትብብር፣ ፍቅርና አንድነት የሚያስፈልገበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።
በስግደት ስነ-ስርዓቱ የተሣተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሀመድ ቡህ ፤ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
መላው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለህዳሴ ግድብ እያሳየ ያለውን ድጋፍና የተባበረ አንድነት በማጠናከር ግድቡን ዳር እንዲደረስ እገዛውን እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅ በሁሉም ዜጎች ዘንድ የፈጠረው መነቃቃት የተሻለ ድጋፍ ለማሰባሰብ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸው፤ "የህዳሴው ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ መግባቱ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለግድቡ የሚያደገውን ድጋፍ እንዲያጎለብት ያስችላል" ብለዋል፡፡
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱም ምክትል ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት ለሀገር ሰላምና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል፡፡
የእምነቱ ተከታዮች "ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የእኔ ነው።" የሚል መልዕክት በጽሁፍ በመያዝ ያላቸውን አጋርነትና ድጋፍ ገልጸዋል።