የግድቡ የግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የጋምቤላ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ የግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የጋምቤላ ነዋሪዎች ገለጹ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ሐምሌ 13/2013 የታልቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም በጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውንም አስታውቀዋል።
ከነዋሪዎቹ መከካል አቶ ጎሳዬ አሰፋ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሁለተኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መላው ኢትዮጵያዊያን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ ሙሌት የድል ዜና የኢትዮጵያን ልማትና እድገት የማይሹ የውጨና የውስጥ ጠላቶችን ያሳፈረ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሻራ ያረፈበት እንደመሆኑ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም የግድቡ ግንባታ አስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል።
የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በተስፋ ሲጠበቁት የነበረ ደስታ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ ኡጌራ አቡቲ ናቸው።
ለግድቡ ግንባታ እንደ ዜጋ በቦንድ ግዥና ገንዘብ መዋጮ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታወሰው፤ "በቀጣይም ድጋፌን አጠናክሬ ለመቀጠል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ቀለሙ ታደሰ በበኩላቸው ፤ የታለቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለሀገር እድገትና ልማት መሰረት በመሆኑ የውሃ ሙሌቱን በስኬት መጠናቀቅ ሲሰሙ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ ሲቃወሙ የነበሩ የውስጥም ሆኑ የውጭ ጠላቶች በቀጣይ ከድርጊታቸው ተቆጥበው የግድቡን ልማት ይደግፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሲሰማ በከፍተኛ ሁኔታ መደሰቱን የተናገረው ደግሞ ወጣት ኪም ጋች ነው።
ቀደም ሲል ተማሪ በመሆኑ ለግድቡ ግንባታ የሚውል የገንዝብ መዋጮ እንዳላደረገ ጠቅሶ፣ በአሁኑ ወቅት አቅም ስላለው ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።