ኢትዮጵያ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ ማራመዷ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንድታጠናቅቅ አግዟቷል- መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ ማራመዷ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንድታጠናቅቅ አግዟቷል- መምህራን
ሀዋሳ ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ መርህ ማራመዷ ጫናዎችን ተቋቁማ የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንድታጠናቅቅ አግዟታል ሲሉ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ መምህራን ገለጹ።
በሃዋሳ ከተማ የታቦር ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር በለጠ ሲጌቦ እንደገለጹት ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷንና ፍትሀዊ የውሃ አጠቃቀም ዓለማቀፍ መርህን መሰረት አድርጋ የምትገነባውን የሕዳሴ ግድብ ለማስተጓጎል ብዙ ርቀት ተጉዘዋል።
"ይሁንና ኢትዮጵያ በምትከተለው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል" ብለዋል።
በጸጥታው ምክር ቤት አሳማኝ የሆነ ሣይንሣዊ ትንታኔ በማቅረብ በመንግት የተሰራው የዲፕሎማሲ ሥራ ጫናውን ከመቀነስ ባለፈ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለዓለም ማህበረሰብ በትክክል ያሳወቀ እንደነበር ለአብነት ጠቅሰዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲቀጥል መወሰኑ እኤአ በ2015 በተደረሰው ስምምንት መሰረት ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
ግብጽ እስካሁን ባደረገቻቸው ሙከራዎች መሸነፏን የገለጹት መምህሩ "ግድቡ ተገንብቶ የተፈለገውን ግልጋሎት መስጠት እስከሚጀምር ድረስ በተለያዩ መንገዶች ለማስተጓጎል ጥረቷን እንደማታቆም ያለፉት ታርኮች ያስረዳሉ" ብለዋል።
እጅ በመጠምዘዝ በቀጣይ ሳንካ ሊፈጥሩ የሚችሉ ያልተጠበቁ የውል ስምምነቶችን ለማስፈረም ጥረት እንደምታደረግ ጠቁመዋል።
"ግድቡ ለአሁንና ቀጣይ ትውልድ የህልውና ጉዳይ ነው" ያሉት መምህሩ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ እያንዳንዱ ዜጋ አስተዋጽኦውን ማበርከት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
በተለይ ምሁራንና በውጭ የሚኖረው ዜጋ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ሙያዊ ትንታኔ በመስጠት በግብጽ ሴራ የተጠለፉ ምዕራባዊያንና ሌሎች ሃገራትን ቀልብ የመመለስ ሚናቸውን እንዲወጡ አመልክተዋል።
አሜሪካና ምዕራባዊያን የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ኢትዮጵያን ሲጫኑ መቆየታቸውን ያስታወቁት ደግሞ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር መምህር ሀብቶም ፈቃዱ ናቸው።
"በተለይ የኢትዮጵያ ማሸነፍና ቀና ማለት ለአፍሪካ ተስፋ መሆኑን ስለሚያውቁ ኢትዮጵያን በማሸማቀቅ የአፍርካዊያንን ህልም ማጨናገፍ ሌላኛው ፍላጎታቸው ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
"ይህን ዓላማቸውን ለማስፈጸም እንደዋና መሳሪያ የሚጠቀሟት ግብጽን ነው" ያሉት መምህሩ ግብጽም ዕውነቱ ጠፍቷት ሳይሆን የግድቡ መገንባት የኢትዮጵያዊያንን የቀደመ ታላቅነት በመመለስ የዓለምን ትኩረት ትወስዳለች ከሚል ስጋት የመነጨ መሆኑን አመልክተዋል።
መንግስት ጫናውን ለመመከትና የኢትዮጵያን ጥቅም ላለማስደፈር ያደረገው ጥረት በሙያዊ ትንታኔ ታግዞ መቅረቡ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን መምህሩ ጠቁመዋል።
"በመላው ዓለም የሚገኙ ዜጎች ለአንድ ዓላማ ያደረጉት ጥረት ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲያሸንፍና የውሃ ሙሌቱ በስኬት እንዲጠናቀቅ አቅም ሆናል" ብለዋል።
የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች የውስጥ ችግሮችን ለማጋጋል እንደሚጥሩ ገልጸው ኢትዮጵያዊያን አሸናፊነትንና ተሰሚነትን ለማስቀጠል ውስጣዊ አንድነትን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
"ጠንክረህ በሰራህ ቁጥር ጠላትህን እያሸነፍክ ትመጣለህ" ያሉት መምህር ሃብቶም በሃገር ውስጥ ምርጫና ሌሎች ኩነቶች እንዲሁም የውጭ የተለያዩ ጫናዎች እያሉ አቋም ተይዞ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መከናወኑ ታሪካዊና ትልቅ ድል መሆኑን አመልክተዋል።
ግብጽን በጥቅም የሚዘውሯት ምዕራባዊያን አሁንም ስለማይተኙ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ከመንግስት ጎን በመሆን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።