አንድነታችንን በማጠናከር የሕዳሴ ግድባችንን ከመጨረሻው ምዕራፍ እናደርሳለን...የኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል ታዳሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
አንድነታችንን በማጠናከር የሕዳሴ ግድባችንን ከመጨረሻው ምዕራፍ እናደርሳለን...የኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል ታዳሚዎች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) አንድነታቸውን በማጠናከር የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከመጨረሻው ምዕራፍ እንደሚያደርሱ የኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አቶ ካሚል ጣሃ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ስኬት እንዳስደሰታቸውና ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
"የሕዳሴ ግድብ የእኛ ሃቃችን ነው" ያሉት አቶ ካሚል፤ ይህንን መብታችንን ተጠቅመን የግድቡን ግንባታ ከመጨረሻው ምዕራፍ ማድረስ አለብን ብለዋል።
የአባይ ወንዝ ለዘመናት ለሌሎች ብቻ ጥቅም ሲሰጥ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ወንዛችንን ለመጠቀም ከጫፍ ደርሰናል ብለዋል።
አገር ስታድግ ሁሉም ተጠቃሚ ስለሚሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
ሼክ መሀመድ ዘይን ሃይረዲን በበኩላቸው የሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ብዙ ፈተናዎች አልፎ ለስኬት መብቃቱን ገልፀው፤ "የግድቡ ግንባታ የመጨረሻው ምዕራፍ እስኪደርስ ድጋፋችንን ማጠናከር አለብን" ሲሉ ተናግረዋል።
ይሄ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት አገራት ተስፋ የሆነ የልማት ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ ሼህ ጣሂር አብዱልቃድር ናቸው።
ስለዚህም ሁለም ኢትዮጵያዊ ባለው ችሎታ፣ ገንዘብ እና ሞራል በመደገፍ የልማት ተስፋችንን ከግብ ማድረስ አለብን ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ትናንት በስኬት መጠናነቁ መገለጹ ይታወቃል።