በጣና ሀይቅ ላይ በጉዞ ላይ እንዳለች የተሰወረችው ጀልባ ካፒቴን አስከሬን ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በጣና ሀይቅ ላይ በጉዞ ላይ እንዳለች የተሰወረችው ጀልባ ካፒቴን አስከሬን ተገኘ
ጎንደር ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) በማእከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በጣና ሀይቅ ላይ በመጓዝ ላይ እንዳለች የተሰወረችው አነስተኛ ጀልባ ካፒቴን አስከሬን መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።
በተሰወረችው ጀልባ አስከሬናቸው የተገኘ ሰዎች ቁጥር 8 ደርሷል።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት በጣና ሀይቅ ላይ 13 ሰዎችን አሳፍራ በጎዞ ላይ እያለች ከተሰወረችው ጀልባ ሰዎችን ለማግኘት በተደረገ የሶስተኛ ቀን ፍለጋ የካፒቴኑ አስከሬን ዛሬ ማለዳ በሃይቁ ማእበል ተገፍቶ ተንሳፎ ተገኝቷል ።
በትናንትናው እለት የ7 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን አስታውሰው አጠቃላይ በጀልባዋ ህይወታቸው ያለፈና አስከሬናቸው የተገኘ ሰዎች ቁጥር 8 መድረሱን ተናግረዋል።
የቀሪዎቹን 5 ሰዎች አስከሬን በአነስተኛ ጀልባዎችና በጠላቂ ዋናተኞች በመታገዝ የማፈላለግ ስራ እንደቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል።
በትናንትናው እለት የተገኘው የሰባት ሰዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቶ የቀብር ስነ-ስርአታቸው እንዲፈጸም መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ጀልባዋ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓም ለሊት 13 ሰዎችን አሳፍራ በወረዳው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቦታ መነሻዋን በማድረግ ወደ ጎርጎራ ወደብ በጉዞ ላይ እንዳለች መሰወሯ ይታወሳል።
የጀልባዋ መነሻና መድረሻ የሀይቅ ላይ ጉዞ የ15 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዳለው ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።