ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ለፍፃሜ እንዲበቃ ሙስሊም ህብረተሰብ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 13/2013 (ኢዜአ) ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለፍፃሜ እንዲበቃ በሚደረገው ጥረት ሙስሊም ህብረተሰብ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ።

1 ሺህ 442ኛው የሂጂራ ኢድ አል አድሃ የአረፋ በዓል በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሃይማኖታዊው ስነ-ስርዓት  በድምቀት  ተከብሯል።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ሙሃመድ በበዓሉ አከባበር ስነ ስርዓት፤ በዓሉን ስናከብር ያለው ለሌለው በማካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በተለይም የረጅም ጊዜ የመልማት ጥያቄያችን ለመመለስ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተጠናቀቀበት ማግስት መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል።

የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚደረጉ ጥረቶችን  በማክሸፍ ግድቡ ለፍፃሜ  እንዲበቃ  ሙስሊሙ ህብረተሰብ አንድነቱን በማጠናከር የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን በማተራመስ እድገቷን ለማቀጨጭ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚደረጉ ትንኮሳዎች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም ብለዋል።

ጥቃቅን ችግሮች ወደጎን በመተው በሀገር ላይ  ሊቃጣ የሚችለውን ትንኮሳ ለመመከት ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል።

 የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል  ከንቲባ ዶክተር ድረስ  ሳህሉ  በበኩላቸው፤ በዓሉን የምናከብረው አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጰያውያን ህዝብ ላይ የቃጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በተዘጋጀንበት ወቅት ነው ብለዋል።

መላው ሙስሊም ህብረተሰብም እንደ ሌሎች የኢትዮጵያዊን እህትና ወንድሞቹ   ከመንግስት ጎን በመቆም በሀገሪቱ ህልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ  ለመቀልበስ   እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል።

''የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተጠናቀቀበት ማግስት በዓሉ መከበሩ ለእኔ ቀኑን የተለየ ያደርገዋል'' ያለው ደግሞ የበዓሉ ተካፋይ ወጣት አብደላ ሰይድ ነው።

በዓሉን በአብሮነትና በሰላም ከማክበር ባለፈ የሀገሪቱ  አንድነት ተጠብቆ  እንዲኖር  መስራት እንደሚገባ ተናግሯል።

ከሶላት ስግደት ማጠናቀቂያ በኋላም ለመከላከያ ሰራዊት፣ ከየክልሉ ለተውጣጡ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሺያ አባላት የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰብ መርሃ ግብር መከናወኑም   ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም