የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መገባደዱ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ፈተና ማለፍ እንደምትችል ማሳያ ነው-- የአሶሳ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መገባደዱ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ፈተና ማለፍ እንደምትችል ማሳያ ነው-- የአሶሳ ነዋሪዎች
አሶሳ፤ ሐምሌ 13/ 2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መገባደዱ ሀገሪቱ የትኛውንም ፈተና ማለፍ እንደምትችል በተግባር ያሳየ መሆኑን በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሰለሞን ክንዴ እንዳሉት፤ የግድቡ ሁለተኛ ውሃ ሙሉት ስኬት ሃገሪቱ የየትኛውም ባንዳ፣ ተላላኪ ወይም ሆነ አማጺ ሴራ እንደማያቆማት ያረጋገጠ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ፈተናዎችን አልፋ ሉአላዊ ሃገር ሆና ህልውናዋን መቀጠሉን ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ግድቡ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን ጂኦ-ፖለቲክስ የመወሰን አቅሟን ያሳድጋል ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅባቸው መደማመጥ ብቻ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
አቶ ኢብራሂም ኑርሁሴን በበኩላቸው፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለህዳሴው ግድብ ከሳንቲም እስከ ሚሊዮን ብሮች አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡
የተለያዩ ሃይሎች ግድቡን ለማደናቃፍ ሲያደርጉት የነበረው ሙከራ ኢትዮጵያውያንን እያበረታታ እልህ ውስጥ መክተቱን ጠቁመው ፕሮጀክቱን እውን እንዲሆን ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
ግድቡን በማገባደድ ለልጆቻችን የሚተላለፍ ታሪክ ሰርተናል ያሉት አቶ ኢብራሂም፤ለግድቡ ፍጻሜ በግላቸውም እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ማንንም እርዳታ አልጠየቅንም ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ዘነበች ታፈሰ የተባሉ ሌላው የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡
የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መገባደድ ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ ሲሯሯጡ የነበሩትን አንገት እንዳስደፋ ገልጸው ኢትዮጵያውያንን ግን በይበልጥ አንድ አድርጓል ብለዋል፡፡
ራዕያችን ተሳክቷል ያሉት ወይዘሮ ዘነበች ፤ በፕሮጀክቱ በመደሰት የገንዘብ፣ ጉልበትም ሆነ የትኛውም ድጋፋችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
አቶ መሃመድ ኡስማን በሰጡት አስተያየት፤ የግድቡ ውሃ ሙሌት አይችሉም ለሚሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንደምንችል በተግባር አረጋግጧል ብለዋል፡፡
ከየትኛውም ሃገር የበታች እንዳልሆን አሳይቷል ሲሉም አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አንድ ባይሆኑ ኖሮ ፕሮጀክቱ ባልተሳካ ነበር ያሉት አቶ መሃመድ፤ ኢትዮጵያን ሊያቆማት የሚችል ሃይል እንደሌለ ግድቡ እንደሚያስረዳ ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለትውልድ የሚተላለፍ እንደሆነ ጠቁመው በልዩነታችን ውስጥ አንድነታንን አጠናክረን ሃገራችን በበለጠ ማልማት አለብን ሱሉ ተናግረዋል፡፡
የመስራት አቅም እና በቂ የተፈጥሮ ሃብት እያለን አንድነታችን በሴራ ተደናቅፎ ወደኋላ ቀርተናል ሲሉ በቁጭት የገለጹት ነዋሪው ካለፈው መማር አለብን ብልዋል፡፡