ቀጥታ፡

በአሁኑ ወቅት የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አለው…የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ  ሐምሌ 12/201 (ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን ከደስታም ያለፈ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

እግር ኳስ ተጫዋች የነበረው ዳንኤል አያሌው የታላቁ የህዳሴ ግድቡ 2ተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በዚህ ቅጽበት ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳልነበረው ተናግሮ የብስራቱ ዜና አስደሳች እንደሆነበት ተናግሯል።

“ለልጆቻችን ትልቅ የተስፋ ብርሃን ነው፤ ወደፊት ኢትዮጵያከፍ የምትልበት ጊዜ የተጀመረ ይመስለኛል” ብሏል፡፡

“ቦንድ ግዝቼ አላውቅም፤ አሁን ግን ባጠራቀምኩት ገንዘብ ሁሉ ለመግዛት ተዘጋጅቻለሁ” ያሉት ደግሞ የሚኒባስ አሽከርካሪው አቶ ደቡሽ ተገኝ ናቸው።

“ግድቡ የኢትዮጵያዊያን ምልክትና የማንነት መገለጫ በመሆኑ እስከመጨረሻው ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት በመክፈል ዳር እናደርሰዋለን” ብለዋል።

የባለሶስት እግር የታክሲ አሽከርካሪው አቶ ኢብሣ ዩሱፍ በበኩላቸው ግድቡ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ዋናው ሚስጥር የኢትዮጵያዊያን ህብረትና አንድነት ብሎም በጋራ መቆም ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

“ግድቡ አላለቀም፤ የግድቡ ዋንጫ ድሬዳዋ ገብቷል፤ ለግድቡ አስተዋጽኦ ለማድረግ አጋጣሚውን በተግባር መጠቀም አለብን” ብለዋል።

“ግድቡ የልማት፣ የነጻነት፣ የማንነትና የህልውናችን ምልክት ነው” ያሉት ደግሞ የቀድሞ አርበኛ የአሁኑ የትምህርት ቤት ጥበቃ ሠራተኛ አቶ አማረ አበራ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት የኢትዮጵያዊያን በሙሉ በመተባበር ጠላቶቹን በማሸነፍ ግድቡን እስከ መጨረሻው በማጠናቀቅ እየተማሩ ለሚገኙ ህጻናት ተስፋና ልማትን ማስረከብ አለባቸው ፡፡

ተመሣሣይ ሃሳብን የሚጋሩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል አቶ ይመር አበጋዝ በበኩላቸው “እኔም ሆንኩ ሁሉም ዜጋ ነገ የተሻለ እድገትና ልማት ለሚያመጣው ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ቦንድ በመግዛትና በገንዘብ አስተዋጽኦ እያደረግን እንገኛለን “ ብለዋል።

ግድቡ ለአሁኑና ለቀጣይ ትውልድ አንገት ሰብሮ ከመሄድ የሚያወጣ በመሆኑ ዜጎች እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ማጠናቀቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ወይዘሮ ፍቅርተ ደመቀ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ቤተሰባቸው በሙሉ ለግድቡ ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ዛሬ የግድቡ 2ተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በጣም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

“የግድቡ ዋንጫ ቤታችን ድረስ መጥቷል፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ብቻ አይደለም ህይወቴን መስዋዕት እስከማድረግ ድጋፍ አድርጋለሁው” ብለዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ከነገው የአረፋ በዓል ጋር ድርብ ደስታ ፈጥሮልኛል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ ናቸው።

በበርካታ ጫናዎች ውስጥ ለምትገኘው ሃገራችን ይሄ ስኬት ከምንም በላይ ከፍ ያለ ትርጉም እንዳለው ገልጸው ወደ ከተማው የገባውን የህዳሴ ዋንጫ ተከትሎ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ነዋሪ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም