ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት የጨዋታ ሜዳውን የቀየረ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል - የታሪክ ምሁራን

ሀምሌ 12/2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት በሌሎች እጅ የነበረውን የመገዳደር ጨዋታ ቀይሮ በኢትዮጵያ ሜዳ ላይ ያደረገበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ሲሉ የታሪክ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መገባደዱ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ውሃው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ የጀመረ ሲሆን ይህ ማለት ግድቡ ሁለት ተርባይኖችን  ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን መያዙን የሚያረጋግጥ ነው።

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተመራማሪና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሰዒድ አህመድ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ወራት ከውስጥና ከውጭ ከፍተኛ ጫና ሲደርስባት መቆየቷን አስታውሰዋል።

ይሁንና አገሪቷ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟትም ሁለት ትላልቅ እቅዶችን ማሳካት መቻሏ ታላቅ ድል ነው ብለዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሠላም መጠናቀቅና የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት የዓመቱ ትላልቅ አጀንዳዎች መሆናቸውን በማስታወስ።

ግድቡ ውሃ ከመሙላት ባለፈ የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ለታለመለት ዓላማ መዋሉ የኢትዮጵያዊያን ጉጉት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህን ጉጉት እውን ለማድረግ ሁለተኛው ዙር ውሃ መሞላቱን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ግድቡ ከዚህ በኋላ "ራሱን የሚጠብቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኪተቦ አብዲዮ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በህልውናቸው የመጣን ጠላት በጋራ መመከት የቆየ እሴታቸው ነው ይላሉ።

በተለይም ግድቡን እውን አያደርጉም፣ አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ እሳቤ "ለዓለም ችለን ማሳየታችን ትልቅ ስኬት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ከታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ጋር የነበራትን አለመግባባት የግድቡን ግንባታ እያከናወነች ለመፍታት ያደረገችው ጥረት አሁን ለደረሰችበት ውጤት እንዳበቃትና ከዚህ በኋላ ድርድሩ በኢትዮጵያ እጅ ላይ መውደቁንም ነው ያነሱት።

የታሪክ ምሁራኑ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲፕሎማሲ ስራ አጠናክራ መቀጠልና የግብጽን ተለዋዋጭ ሴራ በንቃት መከታተል እንዳለባት አስገንዝበዋል።

የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስሟ የሚጠራበትንና መሻገር ያልቻለችውን ድህነት ለማሸነፍ የያዘችው ቁልፍ አጀንዳ መሆኑንም አንስተዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተመራማሪና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሰዒድ አህመድ፡-

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኪተቦ አብዲዮ፡-

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ዛሬ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት መገባደድ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት "ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቁ ውጤት የምንለው ሃይል ማመንጨትና ኤሌክትሪክ ማቅረብ ነው" ብለዋል።

የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በራሱ ትልቅ ውጤት ቢሆንም "ሃይል አመንጭተን ለሕዝባችን  እናቀርባለን" ነው ያሉት።

እንደ ውሃ ሙሌቱ ሁሉ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨቱ ብስራትም በቅርቡ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ደረጃ 80 በመቶ መድረሱም ታውቋል።

ለሕዳሴ ግድቡ ግንባታ እስካሁን ከሕዝብ የተሰበሰበው  የገንዘብ ድጋፍ ከ15 ቢሊዮን  729 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ከግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም