ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያውያንን ድል አድራጊነት ያበሰረ ነው... ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ለኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነትን ያበሰረ መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የመከላከያ ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ በሚሰጠው ትዕዛዝ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ የታላቁ የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ "እንኳን ደስ ያላችሁ" ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትብብር ሠርተዋል ነው ያሉት።

ኢትዮዮጵያውያን የግድቡን ግንባታ የህልውና ጉዳይ አድርገው በልዩ ትኩረት እንደሚከታተሉት የገለጹት ጄነራል ብርሃኑ፤ የሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ "የኢትዮጵያውያንን ድል አድራጊነት ያበሰረ ነው" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ማንንም አገር የመጉዳት ፍላጎትና ዓላማ እንደሌላት ገልጸው፤ የግድቡ የውሃ ሙሌትም ይህንን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ አክለውም የሕወሓት አሸባሪ ቡድን "በከፍተኛ እብሪት የተደራጀ ጦር በመያዝ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በለኮሰው እሳት እራሱ መቃጠሉን ነው" የገለጹት።

መንግስት የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ በወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃም የአሸባሪ ቡድኑን መንግስታዊ መዋቅር ከማፍረስ ባሻገር በበርካታ የቡድኑ ቁልፍ አመራር አባላት ላይ እርምጃ  በመውሰድ ስኬታማ ኦፕሬሽን ማከናወኑን አስታውሰዋል።

ከ46 በላይ የሚሆኑ የአሸባሪ ቡድኑን አመራር አባላት ደግሞ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው የክስ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ነው ብለዋል።

መንግስት በችግር ውስጥ ላሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች አስፈላጊው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስና አርሶ አደሩም ወደ እርሻ ስራ እንዲሰማራ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል መውጣቱንም ጄኔራል ብርሃኑ ተናግረዋል።

ነገር ግን አሸባሪው የህወሃት ቡድን መንግስት ለትግራይ ሕዝብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ በመጠቀም ትንኮሳዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ቡድኑ ለትግራይ ህዝብ ደንታ ቢስ መሆኑና ህዝቡን ለከፋ ችግር ለመዳረግ ቆርጦ መነሳቱን አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ "ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንሄዳለን" በሚል የሚያሰራጨው ከንቱ ፉከራ የትግራይ ህዝብን ይበልጥ ወደከፋ ችግር እንደሚወስደውም ነው የተናገሩት።

 የትግራይ ህዝብ ይህን በመገንዘብ አሸባሪ ቡድኑን "በቃህ ሊለው ይገባል" ያሉት ጄነራሉ፤አሸባሪ ቡድኑ ትንኮሳዎችን የሚቀጥል ከሆነም ሰራዊቱ ከመንግስት በሚሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ በጠንካራ ቁመና ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ  ያለውን ደጀንነት በተግባር እያሳየ መሆኑን የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ፤ ህዝቡ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም