የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት መገባደድ ኢትዮጵያ በስኬት መንገድ ላይ መሆኑዋን የሚያመላክት ነው - ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት መገባደድ ኢትዮጵያ በስኬት መንገድ ላይ መሆኑዋን የሚያመላክት ነው - ፓርቲዎች
ሀምሌ 12/2013 (ኢዜአ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት በስኬት መገባደድ ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆና ስኬትን እየተጎናፀፈች መሆኑዋን የሚያመላክት መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ሙሌት በስኬት መገባደድ ለ"ኢትዮጵያውያን ሁለተኛው የአድዋ ድል ነው" ሲሉም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ሙሌት እንዳታካሔድ የተለያዩ ዓለማ አቀፍ ጫናዎች ሲደርሱባት ቆይተዋል።
በተለይ ወንዙን ለበርካታ ዓመታት በብቸኝነት ሲጠቀሙ የቆዩት ግብጽና ሱዳን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለማሳደር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ የሚገለጠውን ጫና ተቋቁማ ዛሬ የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ይፋ አድርጋለች።
ይህን ተከትሎም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይለ እንገለጹት፤ ሁለተኛው ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በመላው ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገኝ መሆን ተናግረዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ''በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩብንም የግድቡን ሁለተኛ ዙር በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ ለኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ደስታን የሚፈጥር ነው'' ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ሙሌት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የድል ብስራት ከመሆኑም ባሻገር በአካባቢው የነበረውን የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነት ለማርገብ የጎላ ሚና እንዳለውም በአጽንኦት ተናግረዋል።
ግድቡ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አመልክተው፤ የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር ረገድም የማይናቅ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
"ህዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ነው" ያሉት አቶ ሙሉብርሃን፤ በዋናነትም በኢትዮጵያውያን ጉልበት፣ ሃብትና ገንዘብ መገንባቱም የተለየ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረጉን ጠቁመዋል።
የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰይፈሥላሴ አያሌው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በገጠሟት የተወሳሰበ ችግሮች ውስጥ እያለፈች የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ማጠናቀቋ የሚደነቅ እንደሆነም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረችበት ዕለት አንስቶ በተፋሰሱ አገራትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረባትን ጫና ተቋቁማ ለማለፍ እልህ አስጨራሽ ስራዎችን ስታከናወን መቆየቷም ለስኬት እንዳበቃት ጠቁመዋል።
በተለይ ''የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ግድቡ የሚያስገኘውን የጋራ ጠቀሜታ ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያን በጋራ የማደግ ተስፋ ለማጨናገፍ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል'' ነው ያሉት።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ እያንዳንዱ ኢትዮጵያው ጥሪቱን ያፈሰሰበት ከመሆኑ ባሻገር ሁለተኛው ዙር ሙሌት በአገሪቷ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ሕዝብን አንድ በማድረግ ረገድ ትልቅ አጋጣሚን የፈጠረ እንደሆነም አብራርተዋል።
በዛሬው እለት ሁለተኛው ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት መገባደዱ መገለጹ ይታወቋል።