የቻይናው ናሽናል ቢዩልዲንግ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልግ ገለጸ

96
አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2010 የቻይናው ናሽናል ቢዩልዲንግ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የማምረቻ እቃዎችን በማምረትና በግንባታ ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልግ አስታወቀ። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የቻይና ናሽናል ቢዩልዲንግ ኮርፖሬሽን ሊቀ መንበር ሶንግ ዥምፒንግን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። ሶንግ ዥምፒንግ እንዳሉት፤ ድርጅታቸው የማምረቻ እቃዎችን በማቅረብና በግንባታ ዘርፍ መሰማራት ይፈልጋል። ድርጅቱ ከአስር ዓመት በላይ ልምድ እንዳለውና በዓለም ላይ ካሉ 500 ግዙፍ ኩባንያዎች አንዱ መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ በኢትዮጵያም ከጸሃይ ሃይል የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግብዓቶችን ማቅረብ እንፈልጋለን ብለዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቤቶችን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት መገንባት እንደሚፈልጉና ከፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ይሁንታን እንዳገኙ ገልጸዋል። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በውድ ዋጋ ከውጭ የምታስገባቸውን የግንባታ እቃዎች ወጭ ስለሚቀንስ ለድርጅቱ በሩ ክፍት ነው ማለታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዘዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል። ካምፓኒው የራሱን ኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት ወይም በኢትዮጵያ መንግስትና በቻይናውያን በተሰሩ ኢንዱስትሪ ዞኖች በመግባት ስራቸውን ማከናወን እንደሚችሉም ገልጸውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም