ቀጥታ፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል የአገር ሉዓላዊነትና እና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ለሚደረገው ተልእኮ ሽኝት ተደረገለት

ሐምሌ 12/2013 (ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል የአገር ሉዓላዊነትና  የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ለሚደረገው ተልእኮ ሽኝት ተደረገለት።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ባስተላለፉት መልእክት የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ሃይሎችን በጋራ ለመመከት ዝግጁ ነን ብለዋል።

የሕወሃት አሸባሪ ቡድን ለሶስት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያውያንን በአካባቢ፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት የመከፋፈል ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

የቡድኑ እኩይ ዓላማ በተለያዩ አካባቢዎች ሞትና መፈናቀል በማስከተሉ በርካታ ዜጎች ለችግር መዳረጋቸውን አስረድተዋል።

ጁንታው መቀሌ ከመሸገ በኋላም በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብ ላይ የተለያዩ ጉዳቶች መድረሳቸውን አስታውሰዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ተሸናፊ በመሆኑ ከውጭ ጠላት ጋር በማበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁከትና ግጭት ሲፈጥር መቆየቱን አንስተዋል።

የክልሉ ህዝብና መንግስትም  የቡድኑን ተንኮልና ሴራ ተገንዝቦ ከፀጥታ አካላትና ከሰራዊቱ ጋር ተባብሮ  መመከቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የክልሉ ልዩ ኃይል የአገር ሉዓላዊነትና እና የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ለሚደረገው ተልእኮ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ልዩ ሃይሉ ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር ተልእኮውን በብቃት እንደሚወጣም ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ተወካይ ኮሎኔል ፋሲል ይግዛው፤ ልዩ ኃይሉ አገራዊ ጥሪን በመቀበል ለግዳጅ ዝግጁ መሆኑ ለአገሩ ያለውን አለኝታ ያረጋገጠበት አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በግዳጅ ከመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣም አምናለሁ ብለዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል የህወሃትን የሽብር ቡድን ለመመከት የቀረበውን ሀገር የማዳን ኃላፊነት ተቀብሎ በቁርጠኝነት ለመፈፀም ዝግጁ መሆኑን የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የልዩ ሃይል አባላት በበኩላቸው የተሰጣቸውን አገራዊ ግዳጅ በብቃት ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም