በክረምቱ በአባይና ጣና በለስ ተፋሰሶች የጎርፍ አደጋ ስጋት በመኖሩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
በክረምቱ በአባይና ጣና በለስ ተፋሰሶች የጎርፍ አደጋ ስጋት በመኖሩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12/2013 (ኢዜአ) በክረምቱ በአባይና ጣና በለስ ተፋሰሶች የጎርፍ አደጋ ስጋት በመኖሩ ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተጠቆመ።
ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ፣ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን የክረምቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በክረምቱ በተለይ በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የአማራ ክልል የአባይ ተፋሰስና ጣና በለስ ተፋሰሶች ላይ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ይችላል ተብሏል።
በአፋር፣ አዋሽና በጋምቤላ ባሮ ተፋሰሶችም ተመሳሳይ ስጋት በመኖሩ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በመግለጫቸው።
አደጋዎችን ለመቀነስ ተቋማቱ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ገልጸው በተለይም ለቅድመ መከላከል ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በበኩላቸው የጎርፍ አደጋው እንዳይከሰት ከመንግስት 600 ሚሊዮን ብር ተበጅቶ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።
የወንዝ ጠርዞችን የማጠናከር፣ ተፋሰሶችን የማፅዳትና የጎርፍ መከላከያ ስራዎች ከ60 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል በአባይ ተፋሰስ የርብና ጉመር ወንዞች፣ በአፋር ከልል የአዋሽ ወንዝ ተፋሰስ፣ በጋምቤላ ክልል የባሮ ወንዝና ሌሎችም ስራው መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የሰራሽ ግድቦች የውሃ ይዞታቸውን መለካት የተቻለ ሲሆን የጣና በለስ ግን ከአቅም በላይ ሆኖ የሚፈሰው ውሃ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ግድቦቹ በሚሞሉበት ጊዜ በወቅቱ ውሃው መለቀቅ እንዳለበትና በሚለቀቅበት ጊዜም ከታች ላሉ ማህበረሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን መረጃ ቀድሞ ማሳወቅ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
በበጋ ወቅት በወንዝ ዳርቻ የሰፈሩ ወገኖች ክረምቱ መግባቱን ተከትሎ የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስባቸው ከወዲሁ ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ መሰራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን፤ በክረምቱ ዝናብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የአደጋ ስጋት ሊኖርባቸው እንደሚችል ቅድመ ዳሰሳ መደረጉን ጠቁመዋል።
ለዚሀም በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የጎርፍ መከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።
እስካሁንም የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን የማድረስ፣ አደጋ ቢከሰት ዜጎችን መርዳት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች የማመቻቸትና መሰል ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
በክረምቱ ለጎረፍና ተያያዥ ችግሮች 4 ቢሊዮን ብር ሊያስፈልግ እንደሚችል ታሳቢ መደረጉንም ገልጸዋል።