ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ለአላማችን በፅናት ከቆምን ስኬታማ እንደምንሆን ታላቁ ህዳሴ ግድብ ማሳያ ነው - አቶ ርስቱ ይርዳው

ሀዋሳ፣ ሀምሌ 12/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ለአላማችን በፅናት ከቆምንና በአንድነት ከተባበርን ስኬታማ መሆን እንደምንችል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማሳያ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን በማስመልከት  የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።

አቶ ርስቱ በመልዕክታቸው እንዳመለከቱት ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ እኛ ኢትዮጵያውያን ለአላማችን በፅናት ከቆምን፣ አንድነታችንን አጠናከርን በአንድነት ከተባበርን ስኬታማ መሆን እንደምንችል ማሳያ ነው።

የሀገሪቱን መሰረታዊ የኤሌክትሪክ የኃይል ችግር የሚፈታው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር መንስኤ መሆኑንም  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

"በግድቡ ዙሪያ የገጠሙንን ውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች ተቋቁመን ለዚህ ታሪካዊ ቀን መብቃታችን ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል" ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

"መላው የሀገራችንና የክልላችን ህዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ" በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ ህዝብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት እለት ጀምሮ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በአይነትና በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን ጠቅሰዋል።

የግድቡ ግንባታ ከዳር እስኪደርስ ድረስ ህዝቡ ከዚህ ቀደም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ርስቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም