የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መነጋገሪያ እየሆነ ነው

96

ሀምሌ 12/2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅን በሚመለከት በርካታ የአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ባደረጓቸው ድርድርችና ስብሰባዎች ሁሉ ግድቡ የሚሞላው ተፈጥሮአዊ መንገድን ተከትሎ ነው በማለት ሲከራከሩለት የነበረው የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሊት መጠናቀቁን ሜይልኦንላይን ያስነበበ ሲሆን ግድቡን መሰረት ያደረገው ድርድር እስከ ጸጥታው ምክር ቤት መድረሱን አስታውሷል።

ባለፈው አመት የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት መደረጉን በማስታወስ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሲከናወን የነበረው ሁለተኛው ዙር ሙሌት ከሰአታት አሊያም ከደቂቃዎች በኋላ እንደሚበሰር ይጠበቅ ነበር ያለው የፈረንሳዩ ፍራንስ 24 ቴሌቪዥን ግድቡ አሁን ሃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውሃ በመያዙ ሃይል የማምረት ተግባሩ በቅርቡ እንደሚጀመር ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ሰማሁ ሲል ዘግቧል።

ሊጠናቀቅ በተቃረበው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን የገለጸው አልጀዚራ ግድቡ የውዝግብ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን አንስቶ የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን ቦንድ የገዙና የግድቡን መሞላት የሰሙ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም