ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ሲያከብር ለሀገር ሰላምና ህልውና መከበር ወገናዊነቱን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል- አቶ ርስቱ ይርዳው

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 12/2013 -(ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር ከምንግዜውም በላይ አንድነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና ህልውና መከበር ወገናዊነቱን በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው ነገ ለሚከበረው 1ሺህ 442ኛውን የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አረፋ የአንድነትና የአብሮነት በዓላት ከሆኑት አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር የመረዳዳት፣ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት በአሉ መከበሩ አቅመ ደካሞችን በተሻለ ለመደገፍ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ ቀደም ሲል እንደሚያደርገው በዓሉን ሲያከብር የሌላቸውን በማሰብ፣ ማዕድ በማጋራትና አብሮነቱን በማሳየት መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ጫና እየገጠማት መሆኑን ገልጸው "ጫናውን ለመመከት ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል" ብለዋል አቶ ርስቱ።

"ጀግናው መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዐላዊነት ለማስከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መደገፍና ማበረታታት ከሁሉም ይጠበቃል" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የእድገትና የብልጽግና ጉዞ ያላስደሰተው የሽብርተኛው የህወሓት ቡድን የጥፋት ተግባርን ለማስቆም የክልሉ ልዩ ኃይል ከአጋሮቹ ጋር በግዳጅ ላይ መሆኑን አመላክተዋል።

"ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲስተጓጎል እያሴሩ ያሉ የውጭና የውስጥ ሃይሎች ሴራን የእርስ በርስ እንድነትን በማጠናከር ማጎልበት ይገባልም" ብለዋል አቶ ርስቱ።

ሀገራዊ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ ምርጫው በሰላም አይካሄድም ሲሉ ለነበሩ አካላት ሁሉ ትልቅ ሽንፈት መሆኑንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በሀገር ላይ የሚቃጣን አፍራሽ ተልዕኮ አስቀድሞ በመረዳትና አንድነቱን በማጎልበት ማክሸፍ እንዳለበትም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የአካባቢን ሰላም መጠበቅ የሁሉንም ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ህዝቡ በዚህ አግባብ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ሲያከብር ከምንጊዜውም በላይ አንድነቱን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና ህልውና መከበር ወገናዊነቱን በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ ምክትል ርእሰ መሰተዳደሩ አስገንዘበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም