ቀጥታ፡

በመዲናዋ በተሽከርካሪዎች ግጭት ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንገድ ሀብት ጉዳት ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) በ2013 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ባሉት መንገዶች ላይ በተሽከርካሪዎች ግጭት ምክንያት ከ9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ 12 ወራት ውስጥ 62 ግጭቶች በቀለበት መንገድ በሚገኙ ሀብቶች ላይ ሲደርስ 310 ግጭቶች ደግሞ ከቀለበት መንገድ ውጪ በድምሩ 372 የሚሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በግጭት ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙት የመንገድ ሀብቶች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ በተተከሉት የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦችና የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ላይ መሆኑን ነው ባለስልጣኑ የገለጸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መንገዶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ስለሚኖርበት ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ ጉዳት አድራሾቹ ሙሉ በሙሉ እንዲከፍሉ አድርጓልም ተብሏል፡፡

በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በአግባቡ ለማሳለጥ እና የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል መንገዶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ የመንገድ ሀብቶችን ከጉዳት በመጠበቅና በመንከባከብ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ባለስልጣኑ ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም