ከአሜሪካ መንግስት የተለገሰውን "ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን" የኮቪድ-19 ክትባት የጤና ሚኒስትሯ ተረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
ከአሜሪካ መንግስት የተለገሰውን "ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን" የኮቪድ-19 ክትባት የጤና ሚኒስትሯ ተረከቡ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2013(ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የለገሰውን "ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን" የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ ተረክበዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ የክትባት ድጋፉን ቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ለዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።
ዶክተር ሊያ አሜሪካ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ጥረት ስታግዝ መቆየቷን ተናግረዋል።
የክትባት ድጋፉ ወረርሽኙ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና ስጋት አስቀድሞ ለመከላከል በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል ብለዋል።
በተለይም ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችና በበሽታ ሊጠቁ የሚችሉ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ለመለገስ ቃል ከገባችው 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ዛሬ 453 ሺህ 600 ዶዝ ማስረከቧን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።
ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተሰኘው ክትባት በአንድ ዙር ብቻ የሚሰጥ መሆኑ የክትባቱን ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በበኩላቸው አገራቸው ኢትዮጵያ የኮቪድ-19ን ጉዳት ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት ስትደግፍ መቆየቷን ተናግረዋል።
የሕክምና ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያዎችን መለገሷን አስታውሰዋል።
አሜሪካ በቀጣይም ኢትዮጵያ የቫይረሱን ጉዳት ለመቀነስ ለምታደርገው ጥረት የበኩሏን እንደምትወጣ ጠቁመዋል።
አሜሪካ በሚቀጥሉት ሳምንታት 25 ሚሊዮን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ለ49 የአፍሪካ አገራት እንደምትሰጥ ተገልጿል።
በመጀመሪያው ዙር 1 ሚሊዮን ዶዝ ለቡርኪናፋሶ፣ ለጅቡቲ እና ለኢትዮጵያ ተደራሽ ይሆናል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከ277 ሺህ በላይ ዜጎች በኮቪድ 19 የተያዙ ሲሆን 4 ሺህ 350 ዜጎች በወረርሽኙ ሕይወታቸውን አጥተዋል።