ቀጥታ፡

በማይካድራ በህወሓት አሸባሪ ቡድን የተፈጸመው ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እጅግ አሰቃቂ እና ከአእምሮ በላይ ነው...የአካባቢው ነዋሪዎች

ሐምሌ 11ቀን 2013 (ኢዜአ) በማይካድራ በአሸባሪው ህወሓት ቡድን የተፈጸመው ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እጅግ አሰቃቂ እና ከአእምሮ በላይ እንደነበረ ተገለጸ።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ጥቅምት ወር ላይ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን በማጥቃቱ በተወሰደበት አጻፋ በማይካድራ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን አሰቃቂ ጭፍጨፋ ማድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን መገደላቸው ይታወሳል።

አልጄዚራ በቦታው ተገኝቶ የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ እንዳሰራጨው ጭፍጨፋው እጅግ ዘግናኝ እና አረመኔዊ እንደነበር ዘግቧል። የማይካድራ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማሩ ገ/ማሪያም ከአልጄዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ አማራ በመሆናቸው ብቻ በርካታ ሰዎች መጨፍጨፋቸውን ገልጸው፤ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ እጅግ አሰቃቂ እና ከአእምሮ በላይ እንደነበረር ይናገራሉ፡፡

በዚህ ጥቃትም 600 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ቢገለጽም ነዋሪዎች የሟቾች ቁጥር ከተባለው ሊበልጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዘገባው የተካተቱት የአካባቢው ኗሪዋ አንዲት እናት በወቅቱ በልጃቸው ላይ የተለያየ የአካል ክፍሉ ላይ በደረሰበት ጥቃት መስማት የተሳነው ልጃቸው አሳይተዋል፡፡

ከሟቾች ቤተሰብ መካከል አንዲት ባለቤትዋ የተገደለባት በበኩልዋ የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል ሲገድሉት ለምን ትገድሉኛላችሁ ምን አጠፋሁ እያለ ሲጮህ መስማትዋን ተናግረዋል፡፡

ጥቃቱ ከመፈጠሩ በፊት ከተለያዩ የአማራ ክልል ሰራ ለመስራት የሚመጡ ወጣቶች የተለያዩ ጥቃቶች ይደርሱባቸው እንደነበረም ዘገባው ጠቁሟል።

በአሁኑ ሰአት ቦታው በአማራ ልዩ ሃይልና በፌዴራል መንግስት ሃይሎች ቁጥጥር ስር ሰላሙ ተረጋግጦ እንደሚገኝ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ተሰደው በሱዳን መጠለያ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የፌደራል መንግስት ሃይሎች እንዲወጡ እንዳስገደድዋቸው ቢናገሩም በውስጣቸው የማይካድራ ጭፍጨፋ የተሳተፉ አካላት እንዳሉ አልጀዚራ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ማሩ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ምርመራ አድርጎ ባወጣው መረጃ መሰረት በቦታው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደነበረ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም