የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ ገባ
ድሬዳዋ ሐምሌ 11/2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ዛሬ ድሬዳዋ ገባ።
ዋንጫው በሐረሪ ክልል የነበረውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ ዛሬ ድሬዳዋ ገብቷል።
ዋንጫው በድሬዳዋ በሚኖረው ቆይታ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ማስፈጸሚያ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ብር ድጋፍ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
የትውልዱ የማንነት መገለጫ የሆነው ዋንጫ ወደ ከተማዋ ሲገባ በፈረሰኞች ፖሊሶችና በማርሽ ባንድ ታጅቦ አቀባበል ተደርጎለታል።
ከከተማው ሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በተደረገው የአቀባበል ሥነሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ፣የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህና የካቢኔ አባላት፣የአገር ሽማግሌዎች ፣የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል ።
የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የህዳሴው ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ በሚገኝበት ወቅት ዋንጫው ድሬዳዋ መግባቱ ልዩና ታሪካዊ ክስተት ያደርገዋል።
የሀገሪቱና የትውልዱ ልዩ ምልክትና የልማታችን ምሰሶ የሆነው የግድቡን ግንባታ ዳር ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው "የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገው ጉዞ ማሳኪያ ነው" ብለዋል።
"ግድቡ ከሊስትሮ እስከ ባለሀብት ተማሪ እስከ ሊቅ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ተረባርበው የሚገነቡት የኢትዮጵያ ምልክት ነው" ብለዋል።
የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ በስጦታና በቦንድ ግዥ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዋንጫው በአስተዳደሩ በሚኖረው የአምስት ወራት ቆይታ ለግድቡ ግንባታ ማስፈጸሚያ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ ስለመድረሱ የውሀ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።