ቀጥታ፡

“አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን፤ አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን" - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) “አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን፤ አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት የህወሃት ጁንታ ቡድን በርግጠኝነት መልሶ እንዳይበቅል ሆኖ ይነቀላል።

“ይህ የሚሆነው ግን ሁላችንም እንቦጩን ለመንቀል ከተረባረብን ነው፤ በሂደቱ ውስጥ እዚህና እዚያ ግለሰቦች ሊሳሳቱ ይችላሉ፤ ሐሳብ የሚከፋፍሉ መረጃዎች ሊሰሙ ይችላሉ፤ በግብ አንድ ሆነን የአካሄድ ክርክር ይፈጠር ይሆናል " ብለዋል።

“ የገጠምነው ጠላት የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነውን ጠላት ነው፤ ጁንታው ያገኘውን የፖለቲካ ሥልጣን የገዛ ሀገሩን ለማፍረስ የተጠቀመ ምናልባት በታሪክ ብቸኛው ቡድን ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

"በሀገራችን አረም በደቦ ነው የሚነቀለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የኢትዮጵያ ልጆችም እርሱን እያደረጉት ነው“ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን የጁንታውን ዕቅድ ለመቀልበስ መነሳታቸውንና ይህ በራሱ ድል መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ይህ አንድነታችን ያስፈራቸው ኃይሎች የሚከፋፍል የመሰላቸውን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ፤ ዓይነ መዓታችንን ከእነርሱ ላይ አንሥተን በገዛ ወገኖቻችን ላይ እንድንተክል ያሤራሉ፤ ፈጽሞ አናደርገውም “ ብለዋል።

የመከላከያ ኃይልና የክልል ኃይሎች ተገቢውን ቦታ እየያዙ መሆኑንና ያንን ለማወክ ትንኮሳ እንደሚኖር ገልጸው፤ ለዚህም ቃል የተገባውን የተኩስ አቁም እየተጠበቀ ተገቢው ምላሽ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

“ምንን፣ ለምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ ማድረግ እንዳለብን ጥብቅ ዕቅድ አለን ፤ ውጤቱን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወዳጅም ጠላትም ያየዋል፤ ሠራዊታችን አስፈላጊ ሲሆን እጅን በአፍ ላይ ለሚያስጭን ተልዕኮ ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም