የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ውጤት ያለው ለውጥ ማምጣት አለበት -ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ውጤት ያለው ለውጥ ማምጣት አለበት -ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አዳማ፤ ሐምሌ 11/2013(ኢዜአ).. የበጎ ፍቃድና የዜግነት አገልግሎት በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ውጤት ያለው ለውጥ ማምጣት በሚቻልበት መልኩ መከናወን አለበት ሲሉ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በአርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ በመገኘት የአረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩበትን ችግኝ በመትከል የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር አስጀምረዋል።
ሚኒስትሯ በወቅቱ እንደገለፁት የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በህብረተሰቡ ህይወት ላይ ውጤት ያለው ለውጥ ማምጣት አለበት።
በተያዘው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ሺህ በላይ ችግረኞችን ከጎዳና ለማንሳት መታቀዱን የገለጹት ዶክተር ኤርጎጌ "አረጋዊያንን መንከባከብ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስና አፍርሶ መስራት ላይ ትኩረት አድርገናል" ብለዋል።
የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ትናንት በአርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩበትን ችግኝ በመትከል የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት በማስጀመር መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ሚኒስቴሩ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እስከ ወረዳ ድረስ ያሉትን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ መስሪያ ቤቶችን በማስተባበር የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱን አመልክተዋል።
የአረጋዊያን እንክብካቤና ድጋፍ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ጎዳና ላይ የወጡ ህፃናት ጨምሮ ዜጎችን ከጎዳና ማንሳት፣ እንዲሁም በቁሳቁስ መደገፍና ማገዝ ደግሞ በመርሀ ግብሩ በዋናነት የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚከናወኑ ስራዎች በተጨማሪ በተያዘው 2014 በጀት ዓመት ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ለማንሳት መታቀዱን አመልክተዋል ።
የሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሰሁን ፎሎ በበኩላቸው ኮንፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያን እናልብሳት መርሀግብር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮንፌዴሬሽኑ ሰራተኞች በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ ተገኝተው ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ለአብነት አንስተዋል ።
የሠራተኞችና የአሰሪዎች ፌዴሬሽንና ሚኒስቴሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሀገሪቷ ሁሉም ክልሎች በጎ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው "በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ መሰረት የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በተናጠል ሳይሆን ተቀናጅተን ተሳትፎ እያደረግን ነው "ብለዋል።
በኢትዮጵያን እናልብሳት መርሀ ግብር ችግኝ ተከላ ፣ የአቅም ደካሞችን ቤት በማደስና በመጠገን እንዲሁም በሌሎች ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጮሌ ወረዳ ትናንት በተካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።