ቀጥታ፡

ንግድ ባንክ በ13ኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ማበረታቻ ሽልማትን ያሸነፉ 49 እጣ ቁጥሮችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ነሀሴ 1/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ13ኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ማበረታቻ ሽልማትን ያሸነፉ 49 እጣ ቁጥሮችን ይፋ አደረገ። ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ያዘጋጀው 13ኛው ዙር ይቀበሉ ይሸለሙ የአይነት ሽልማት እጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት ዛሬ በአዲስ አበባ ብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ አካሂዷል። ባንኩ  ከግንቦት 15 እስከ ሐምሌ 14 ቀን 2010 ዓ.ም  የውጭ ምንዛሬ የዘረዘሩ ደንበኞች ብቻ በተካተቱበት መርኃ ግብር አንድ 13 ሰው የሚጭን ሚኒባስ ተሽከርካሪ ፤16 የውሃ ማጣሪያዎችና 32 ዘመናዊ የስልክ ቀፎዎችን በአጠቃላይ 49 አሸናፊ እጣዎችን ለእድለኞች ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረትም አንደኛ እጣ 13 ሰው የሚጭን ሚኒባስ የሚያስገኘው እጣ ቁጥር 6616578 ሆኖ ወጥቷል። በተለያዩ መንገዶች አሸናፊዎች እንደሆኑ በማስመሰል በሐሰት ለማታለል የሚሞክሩ ግለሰቦች ስለሚኖሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁሉም እድለኞች አንደሚያሳውቅም ባንኩ ገልጿል። በባንኩ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጢቆ እንደተናገሩት ባንኩ በኃብት ማሰባሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት  ለኢኮኖሚያዊ እድገት የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። በዚህም ህብረተሰቡ የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብርና በባንክ በኩል የሚያደርገውን የውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚነት ባህል ለማዳበር የማበረታቻ ፕሮግራሞችን ነድፎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። መንግስት የውጭ ምንዛሬ ያላቸው ግለሰቦች በባንክ ሄደው እንዲዘረዝሩ ጥሪ ካቀረቡ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ገንዘብ እየተዘረዘረ ይገኛል ብለዋል። ከመንግስት ጥሪ በተጨማሪም ባንኩ የሚያዘጋጃቸው የማበረታቻ ሽልማቶች የውጭ ምንዛሬዎችን ለማግኘት ከፍተሻ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው አቶ ለገሰ የተናገሩት። ይህ 13ኛው ዙር የይቀበሉ ይሸለሙ የማበረታቻ ሽልማትም ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በርካታ የውጭ ምንዛሬ ወደ ባንኩ መጥቶ መዘርዘሩንም ገልጸዋል። በዚህም በባንኩ የውጭ ምንዛሬያቸውን እየመነዘሩ ለሚገኙ ደንበኞች ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዳይሬክተሩ ሌሎችም በቀጣይ በሚዘጋጁ መርኃ ግብሮች ወደ ባንኩ መጥተው በመመንዘር እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም